የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የወጪ ንግድ ምርትን ለማሳደግ ጉልህ አበርክቶ አለው-የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን

137

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የወጪ ንግድ ምርትን ለማሳደግ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው የፌዴራል ሱፐርቪዥን ተቋማት ቡድን ገለጸ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ላሞች ማዳቀል መቻሉን እና 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሊትር ወተት ምርት መገኘቱን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።


 

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ተመልክቷል፡፡


 

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶክተር ዮሐንስ ግርማ እንዳሉት፥ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በዶሮ፣ ወተት፣ ዓሳና ማር ምርት ላይ ለውጥ መጥቷል።

መርሐ ግብሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የወጭ ንግድ ምርትን ለማሳደግና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ዓላማ አድርጎ በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።

የወተት ምርትን ለማሳደግ የአገረሰብ፣ የተዳቀሉና የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን ላሞች ምርታማነት ለማሳደግ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በ2015 በጀት ዓመት የተሻሻሉ ላሞች 500 ሺህ እንደነበሩ ጠቅሰው  በታየዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ላሞች ማዳቀል መቻሉን አስረድተዋል። 

በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሊትር ወተት ምርት መገኘቱን በመግለጽ።

በዶሮ እርባታ ላይም የተሻሻሉ ዝርያዎችንና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ በኩል አበረታች ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።  

በ2014 ዓ.ም የተሰራጨው የ1ቀን ጫጩት 28 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው የሌማት ቱሩፋት ከተጀመረ በኋላ በመጣው ለውጥ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 57 ሚሊዮን መሰራጨቱን ገልፀዋል። 

የማር ምርትን ለማሳደግ የንብ ቀፎዎችን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ የማሻሻል ስራ መሰራቱን ጠቅሰው የሌማት ትሩፋት ከመጀመሩ በፊት 250 ሺህ የነበረው ዘመናዊ የንብ ቀፎ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ1 ሚሊዮን መሻገሩን አብራርተዋል።

ዘመናዊ የንብ ቀፎ በአንድ ጊዜ 30 ኪሎግራም የማር ምርት የሚያስገኝና በዓመት ለሶስት ጊዜ ተመሳሳይ የማር ምርት ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ወጣቶች ተደራጅተው የውሃ አካላትን በመንከባከብ በዓሳ እርባታ እንዲሰማሩ ለማስቻል የቴክኖሎጂ ድጋፍና የጫጩት ማባዣ ማዕከላትን አቅም ማሳደግ ላይ እየተሰራ እንደሚገኝም እንዲሁ።

አሁን ላይ የዓሳ ጫጩት ማሰራጨት ስራ ከነበረበት 1 ሚሊዮን ወደ 5 ሚሊዮን መሻገሩንም አንስተዋል።


 

የቦሌ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጆቴ በበኩላቸው፥ ነዋሪዎችን በከተማ ግብርና ላይ በማሳተፍ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም በዶሮና እንስሳት እርባታ፣ የማርና ወተት ምርት እንዲሁም የጓሮ አትክልት ስራዎች ላይ ተሰማርተው በምግብ ራሳቸውን በመቻል ለገበያ ምርት ማቅረብ ላይ እየደረሱ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዳይሬክተርና የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባል አቶ አብዱልፈታ የሱፍ፥ ቡድኑ በሌማት ትሩፋት የተከናወኑ ስራዎች የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና የተሟላ ስርዓተ ምግብ እንዲኖር አስተዋፅኦ እንዳለው  በመስክ ምልከታው ማረጋገጡን ተናግረዋል።

የተሻሻሉ የእንስሳትና የዶሮ ዝርያዎችን በማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ በኩል እየተሰሩ ያሉ ተግባራት መኖራቸውን መመልከታቸውንም ገልፀዋል።

ይህም የግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪው በቂ ግብዓት የሚያቀርብ፣ የወጪ ንግድ ምርትን የሚጨምር እና ለበርካታ ዜጎች የስራ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን አይተናል ነው ያሉት።

የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድኑ በሌማት ትሩፋት የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ ማስፋት  እንደሚገባም አሳስቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም