የሕብረት ሥራ ማህበራት በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል -አቶ እንዳሻው ጣሰው

124

ሆሳዕና ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረት ሥራ ማህበራት በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ የአመራርና የአደረጃጀት ማሻሻያ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

“ህብረት ስራ ማህበራት ለዘላቂ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ የሕብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

በስነስርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት፣ ማህበራቱ በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማርገብና የአባሎቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አላቸው።

በገበያ የዋጋ መናር በህዝብ ላይ ጫና እንዳይፈጥር የግብርናና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ እያበረከቱት ያለው አስተዋጾ ላቅ ያለ መሆኑንም ጠቅስዋል።


 

ማህበራቱ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህ ተግባራት የማህበሩን አባላትና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ያሳድጋሉ ብለዋል።

ማህበራቱ በብቁ ባለሙያ እንዲመሩ፣ አሰራራቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲያስደግፉ እንዲሁም የፋይናንስ ግልጸኝነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው እንዳሉት ህብረት ሥራ ማህበራቱ ከቆይታቸውና ከአባሎቻቸው ብዛት ጋር ሲነጻጸር ብዙ ማደግ ሳይችሉ ቆይተዋል።

ይህን በመለወጥ ጠንካራና ሀገራዊ ሚናቸውን ለማጉላት ችግሮቻቸውን ፈቶ በተጠና መንገድ ለማዋሀድና ተቀናጅተው እንዲሰሩ ለማድረግ ማሻሻያው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

"ለማሻሻያው ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የአደረጃጀት፣ የአመራርና የአሰራር እንዲሁም የፋይናንስ ክህሎት ችግሮች ይጠቀሳሉ" ያሉት አቶ ሺሰማ፣ እነዚህ ችግሮች ሲፈቱ የአገልግሎት አቅማቸው ይሰፋል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት፣ በክልሉ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ 5 ሺህ 600 የሕብረት ስራ ማህበራት አሉ።

ማህበራቱ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳላቸው ጠቁመው፣ እነዚህ ማህበራት የተሻሻለ ቴክኖሎጂን በማቅረብ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ በገንዘብ ቁጠባና ብድር እንዲሁም ገበያን በማረጋጋት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበራቱ በክልሉ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጾ ከዚህም በላይ ለማሳደግ በአዲስ መልክ ተዋህደውና ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በክልሉ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ተሳትፈዋል።

ከንቅናቄ መድረኩ ጎን ለጎን የግብርና ምርቶች ለሸማቹ የቀረበበትና ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ባዛር በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ተከፍቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም