በብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው

129

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ በብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የብሪክስ ጥምረት 10 አገራትን በማቀፍ 37 በመቶ የኢኮኖሚ እና 45 በመቶ የዓለም አቀፍ የህዝብ ቁጥር የሚሸፍን ግዙፍ የትብብር ጥምረት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የጥናትና ምርምር ተቋማት የባለሙያዎች ቡድን በብሪክስ ጥምረት ስር ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል የምክክር መድረክ  በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ በመድረኩም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸው ምሁራንና የምርምር ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ በሩሲያ ሊቀመንበርነት የሚመራው የብሪክስ አባል አገራት ጥምረት የመሪዎች ጉባኤ በመጪው ግንቦት ወር በሩሲያ ሞስኮ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

መድረኩም በመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ መፍትሔ አመላካች አጀንዳዎች ላይ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ የሚያቀርቡበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

እነዚህ ሃሳቦችም በመሪዎች አማካኝነት የጥምረቱ የጋራ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ባለሙያዎችም ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ በብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሩሲያ የብሪክስ ምክር ቤት ኃላፊ ቪክቶሪያ ፓኖቫ (ዶ/ር)፤ በብሪክስ ማዕቀፍ ስር የሚካሄዱ የምክክር መድረኮችም ለመሪዎች ጉባኤ ውሳኔ የሚበጁ ምክረ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል። 


 

በብሪክስ አባል አገራት መካከል የሚደረገው ትብብር ከጥምረት ባሻገር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚበጁ ችግር ፈቺ ሃሳቦች እንዲተገበሩ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡

በመድረኩም የኢትዮጵያ ምሁራንም ከሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም በመነሳት የብሪክስ አባል አገራትና ቀሪውን ዓለም የሚጠቅም የጥናት ውጤት እንዲያቀርቡ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ጨምሮ ከሁለቱ ሀገራት የጥናትና ምርምር ተቋማት የተወከሉ ምሁራን ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የብሪክስ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ በአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ፣ በግብርና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል። 

በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ  ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የብሪክስ አባልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም