በክልሉ አዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ የግንዛቤ ሥራዎችን መስራት ይገባል - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

114

ቦንጋ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉን ያሳተፈ ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር በቅርቡ በጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 አስፈላጊነትና ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ገለጻ ተደርጓል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት በክልሉ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉን ያሳተፈ ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

በክልሉ በኪራይ ቤት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ አዋጁ የተከራይና አከራዩን መብት ከማስጠበቅ ባለፈ መንግስትም ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአከራይና ተከራይ መካከል ሲፈጠሩ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ስለሚሰጥ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ለተግባራዊነቱ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ የማታዓለም ቸኮል በበኩላቸው ቢሮው ለአዋጁ ተፈጻሚነት የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልፀዋል።

በቀጣይ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩ የገለጹት ሀላፊው፣ በየደረጃ ያሉ ባለድርሻ አካላትም ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመድረኩ የአዋጁ ዝርዝር ሀሳቦች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተግባራዊነቱ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አዲሱ የመኖሪያ የቤት ክራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ምክንያታዊና ፍትሀዊ ያልሆኑ የቤት ኪራይ ጭማሪዎችን እንደሚያስቀር ተመላክቷል። 

 መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የጸደቀው  አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም