ነገረ - አስተውሎት

(በሰለሞን ተሰራ)

ሰው በሀሳብ ከሕይወታዊያን ፍጥረት ይለያል። ከፍጥረቱ ጀምሮ ኑሮውን ቀላል ለማድረግ አስቧል። ሀሳቡም መላ ፈጥሯል። ድንጋይ አፋጭቶ እሳትን አንድዷል። እንስሳትን አላምዶ፣ ሰብልን አባዝቶ፣ መጠለያውን ቀልሶ… ኑረቱን አሳልጧል። ዕለታዊ ተግባሩን ለማቃለል በቁስ ላይ ተመራምሮ አጋዥ ቁስ ፈጥሯል። በሂደትም የኢንዱስትሪን አብዮት አፈንድቷል። 

በ18ኛው ክፍለ ዘመን በባተው የኢንዱስትሪ አብዮት ዓለም አዲስ ክስተት አስተናግዳለች። ፋብሪካዎች፣ መኪናና አውሮፕላን፣ የእንፋሎትና የኤሌክትሪክ ኃይልና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች ተፈብርከው ምርትና ምርታማነት ጨምሯል። ከተሜነት አብቧል። የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ አውቶሜሽን፣ ሮቦቲክስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በሰው ተፈጥረዋል። 

ሳይንስን ለመፍትሔ-እንከን አውሏል። ቴክኖሎጂን ለሁለንተናዊ ሕይወት ማቃለያ ተጠቅሟል። ጊዜ፣ ጉልበትና ሀሳብን ከፈጠራ ጋር አዋዶ ኑሮና ሕይወት አቅልሏል። ኮምፒዩተር ፈበረከ፤ ኢንተርኔትን ፈጠረ፣ ዓለምን አስተሳሰረ። የተዓምር ዘመን ሆነ።

ሰው እያስተዋለ... እያስተዋለ… በረቀቀ ጥበብና ግኝት ዛሬ ከዘመነ-አስተውሎት ደረሰ። ሰው ሰራሽ አስተውሎት!!

የዘመኑ ቴክኖሎጂ ልህቀት ደረጃ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) እንደሆነ ይጠቀሳል። ዳሩ የቴክኖሎጂው እምርታ የዘመን ክስተት ሳይሆን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ጀምሮ እርሾ ሲያቦካ እንደነበር የዘርፉ ምሁራን ይጠቅሳሉ። 

ዋረን ማክኩሎች እና ዋልተር ፒትስ ለዛሬው ሰው ሰራሽ አስተውሎት እርሾ የሆነ በነርቭ አውታረ መረብ የሚታገዝ ሒሳባዊ ሞዴል የፈጠሩት በ1943 ዓ.ም ነበር። በ1950 ዓ.ም ደግሞ አለን ተርኒግ እንደ ሰው ማሰብ የሚችል ማሽን ፈለሰፈ። በተመሳሳይ በ1960ዎቹ አጠቃላይ ችግር ፈቺ፣ ሎጂክ ቴዎሪስትና መሰል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞች በልፅገዋል።

በ1950 ዓ.ም ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ራሱን ችሎ እንዲጠና ተወሰነ። ለውስብስብ ችግሮች አይነተኛ መፍትሄ መሆኑ ታመነበት። በ1970 እና 80ዎቹ የዘርፉ ሊቃውንት የሰውን ልጅ የመወሰን አቅም የሚተካ የኮምፒውተር ፕሮግራም ለማበልጸግ ጥረት አድርገዋል። በ1990ዎቹ ምርምሮቹ መቀዛቀዝ ጀምረው ነበር። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳግም አንሰራርቷል። ስልተ ቀመርን (algorithm) የሚረዱ ማሽኖች ስራ ላይ ውለዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የጥናት ዘርፍ የሰውን ስራና ሃሳብ በኮምፒዩተር መራሽ ቁሶች መተካት ነው። የሰው ልጅ ፍጥረት የሆኑ ማሽኖች መገንዘብ፣ መማርና ችግሮችን እንዲቀርፉ ማስቻልም ነው። ማሽኖች በሰው ልጅ ምትክ አካባቢን ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድና መፍጠር፣ መተንተንና እንከኖችን ማምከን እንዲችሉ ማድረግ ነው። የሰውን የማሰብ ኅይል በኮምፒዩተር አዳብሮ በሰውኛ ጥበብ ሕይወትን ማቅለል ነው። 

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ ያሉትን የስሜት ህዋሳት ክህሎቶች ለማሽኖች በማስተማር ሰዎች ነገሮችን በቀላሉ እንዲያገኙና እንዲተገብሩ ማስቻል ነው። በዚህም የኮምፒውተር ሊቃውንት ስልተ ቀመር ወይም አልጎሪዝምና አስበው የሚሰሩ ማሽኖች ወደ ስራ እያስገቡ ነው።

ለአብነትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥበብ ቤት የሚያጸዱ ሮቦቶች፣ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች፣ ሰው አልባ ጦር መሳሪያዎች፣ የደህነንት ጥበቃ ካሜራዎች፣… በልጽገው ስራ ላይ ውለዋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጀመረው ይህ ቴክኖሎጂ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተስፋም ስጋትም ይዞ መምጣቱ ይነገራል። 

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዛሬ ላይ በሁሉም መስክ ገቢራዊ እየተደረገ ነው። በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ በደህንነት፣ በግብርና ዘርፎች ምርትና አገልግሎትን ለማቀላጠፍና ለመጨመር ቁልፍ አማራጭ ተደርጓል። ቴክኖሎጂው ከዓለም ገበያ ከ350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድርሻ አለው።

አፍሪካም እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፍ  የሰው ሰራሽ አስተውሎት ገበያ 10 በመቶ ድርሻ  መያዝ ከቻለች እኤአ  2030 አሁን ያለው አህጉራዊ ጥቅል ምርቷ (ጂዲፒ) 50 በመቶ ይጨምራል።

ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት ዘርፉን የሚመራ ተቋም መስርታለች፤ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን። ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምህዳር ተጠቃሽ ሀገር ለማድረግ አበክሮ እየሰራ ነው። በቅርቡ የተመረቀው “አስተውሎት” የተሰኘ ፊልም ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሰው ልጅ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የማይገባበት ሕይወት እንደሌለ ፊልሙ ያስረዳል። በጤና፣ በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ በመረጃ ፍለጋ፣ በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በግብርና፣ በማዕድን ፍለጋና፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የዚህ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና ተንጸባርቋል።

ዘርፉ ከቅንጦት ይልቅ አስፈላጊነቱ ጨምሯል። ለበሽታ መከላከል፣ ለጤና እንክብካቤ፣ ለትምህርት መሻሻልና ድህነት ቅነሳ ይውላል። ለዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎች ፈጠራና አቅም እያደገ መምጣቱ በፊልሙ ተገልጿል። ፊልሙ የኢትዮጵያ የቡና ዛፎችን የበሽታ ስርጭት ለይቶ ለማከም ያለውን ውጤታማነት ያወሳል። 

ሰው ሠራሽ አስተውሎት የአገራችንን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የሳይበር ደህንነትን ለመጠበቅ፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ ምርታማነትን ለመጨመር፣ ገበያን ለማስፋት እና ለመሳሰሉት ሥራዎች በእጅጉ አስፈላጊ ነው። 

በአሁኑ ወቅት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ እየተስፋፉ ከሚገኙ አገልግሎቶች መካከል ማሽን ትራንስሌት ወይም የቋንቋ ትርጉም አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያም አንዱን ቋንቋ ወደ ሌላ በመተርጎም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም በአንድ መተግበሪያ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን መማር እንዲሁም ከድምጽ ወደ ጽሁፍ መቀየር የሚያስችል ሥርዓትን አበልጽጎ ለተጠቃሚዎች አቅርቧል። 

መተግበሪያው አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎችን በድምጽ እና በጽሁፍ ለመማር የሚያስችል ሲሆን ድምጽን ወደ ጽሁፍ መቀየር የሚያስችለው የመተግበሪያው አካል ድምጽን በመቅዳት ወይም ከመዛግብት (አርካይቭ) የድምጽ ፋይሎችን ወደ መተግበሪያው በማስገባት የጽሁፍ ቅጂውን ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ከፊልሙ መገንዘብ ተችሏል።

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የደረሰበትን ልህቀት ያማከሉና ከዘርፉ ውጤት ለማግኘት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተኬደው ርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልህቀት በመመልከት ሀገራችንን የሚመስሉ የዘርፉን ውጤቶች የበለጠ ማላቅ ያስፈልጋል።

በዓለም የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ውስጥ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እያሳደረ የሚገኘውን ተጽዕኖ በመረዳት ለዘርፉ ምርምሮች የሚደረገውን ድጋፍ የበለጠ ማጠናከር ያሻል። ዓለም የሚሄድበትን ፍጥነት በመመልከት ሀገራችንን የሚመስሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን ለመተግበር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም