በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል

117

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ  የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

"ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ አውደ ርዕይና ባዛር ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለውጪ ንግድ፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት በስራ እድል ፈጠራ ለውጥ እያስመዘገበ ነው፡፡

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ  ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም ዜጎች በሀገራቸው ምርት እምነት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ የአመለካከት ለውጥ እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

አውደ ርዕይና ባዛሩም አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኝ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች 81 አውደ ርዕዮች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ አምራችንና ሸማቹን በማገናኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው በመዲናዋ ከ3 ሺህ 700 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት 42 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመቅረፍ ረገድ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ በተከፈተው አውደ ርዕይና ባዛር  ከ200 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ለአራት ተከታታይ ቀናት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም