ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር እየሰራች ነው- አምባሳደር አባቢ ደምሴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክም አጠናክሮ ለመቀጠል እየሰራች መሆኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር  ጄነራል አምባሳደር አባቢ ደምሴ ገለጹ።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ-ኬንያ  ባለሀብቶች የቢዝነስ ፎረም ላይ ነው።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በታሪክ፣ በህዝብ ለህዝብና ሌሎችም ማህበራዊ እና  ኢኮኖሚያዊ  መስኮች ረጅም ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንዳላቸው እንስተዋል።

ሁለቱም ሀገራት ለሁለንተናዊ እድገት በቅንጅት እየሰሩ ነው ያሉት አምባሳደር አባቢ፥ የማህበራዊ መስተጋብሮች መጠናከር ለኢኮኖሚያዊ እድገት መሳለጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የሀገራቱ የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ  ጠንካራ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ እና  የኬንያ መንግስታት ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር ስምምነቶችን መፈራረማቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለማሻገር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን አስረድተው፥ የሁለቱ ሀገራት ባለሃብቶችም በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንግስት ኢንቨስተሮችን  በግብርናው፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በአይሲቲ ለመሳብ ምቹ የንግድ አካባቢን  እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የኬንያ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኬኒያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና በበኩላቸው በፎረሙ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ከምንጊዜውም በላይ ለማጠናከር የሚያስችል ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

ኬንያውያን በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚያስችላቸውን ምቹ ዘርፎች የሚለዩበት ዕድል መጠፈሩን አንስተዋል።

በተመሳሳይ ፎረሙ ኢትዮጵያዊያን በኬንያ ምቹ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎችን እንዲያውቁ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል

ኢትዮጵያና ኬንያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ ለመሆን እርስ በእርስ ያላቸውን የንግድ ልውውጥ በማጠናከር የትብብር ስራቸውን ያስቀጥላሉ ብለዋል።

የአዲሰ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ  መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማጠናከር ባለሃብቶች ልምድ ለውውጥ የሚያደርጉበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም