ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር እና ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ለብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ የሚውሉ መሳሪያዎች ግዥ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር እና ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ለብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ የሚውሉ መሳሪያዎች ግዥ ስምምነት ተፈራረሙ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ባንኮች ማሕበር የቦርድ ሊቀመንበር አቤ ሳኖ እና የላሚኖ ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ቅዱስ ገብረስላሴ ስምምነቱን ፈርመዋል።

አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ውቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፥ 32 ባንኮች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 6 ሺህ የምዝገባ ቁሳቁሶችን መግዛት የሚያስችላቸው ነው።

በስምምነቱ መሰረት ላሚኖ ኢንጂነሪንግ የምዝገባ ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ በሚገኙ 11 ሺህ የባንክ ቅርንጫፎች በመጀመሪያው ዙር 40 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ  ተጠቃሚ  የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ዜጎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች በመሔድ የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የላሚኖ ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስከያጅ ቅዱስ ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ቁሳቁሶችን በተባለው የጥራት ደረጃና በተቀመጠው ጊዜ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የምዝገባ ቁሳቀሶቹ በፍጥነት ተሟልተው ወደ ስራ ሲገባ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ለማፋጠን ሚናው የላቀ እንደሚሆን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዩዳሔ አርዓያ ስላሴ ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት በተሳሳተ ማንነት የሚያጋጥማቸውን የማጭበርበር ወንጀል የሚቀንስ እና አገልግሎታቸውንም ቀልጣፋና ተዓማኒ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የዲጅታል መታወቂያ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ግልፅነትና አካታችነትን ለማጎልበት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም