በክልሉ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት የተሳለጠ የፍትህ አሰጣጥን ማጎልበት ይገባል

147

ሐረር፤ ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ፍርድ ቤቶች  ላይ  የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት የተሳለጠ የፍትህ አሰጣጥ ማጎልበት እንደሚገባ  የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  ሱልጣን አብዱሰላም አስገነዘቡ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ ያለውን የፍትህ አስተዳደር ሪፎርም በክልሉ በሚተገበርበት ሁኔታና ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ለህዝቡ የተሳለጠ ፍትህ ለመስጠት በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።

ፍርድ ቤቶቹ በሚያከናውኗቸው የፍትህ አሰጣጥ  ሂደት ላይ ጠንካራ የሆኑ አሰራሮች ቢኖሩም ውስንነቶችም እንደሚታዩ አልሸሸጉም።

በተለይም በክልሉ ፍርድ ቤቶች ላይ ከፍትህ አሰጣጥና  ከሌሎች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ለህብረተሰቡ የተሳለጠ የፍትህ አሰጣጥ መስጠት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከዚህም ባለፈ ህብረተሰቡ የሚተማመንበትና እውነተኛ ፍትህ የሚያገኝበት ፍርድ ቤቶችን መገንባት እንደሚገባ በማከል።  

እንደ አፈ ጉባዔ ሱልጣን ገለፃ መድረኩም በፍርድ ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመለየት እገዛ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ እየተሰሩ ያሉ የፍትህ አካላት ሪፎርምን በክልሉም ተግባራዊ ለማድረግ ፍርድ ቤቶቹ፣ ከዐቃቤ ህግ፣ ከፓሊስና ማረሚያ ቤቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይኸም እስከታችኛው የእርከን ደረጃ እንዲወርድ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት የህግ አስተዳደር፣ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኢማን መሐመድ በበኩላቸው ከፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ መድረኩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በተጨማሪም  በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ የፍትህ አሰጣጡና አሰራሩ እንዲሁም ከህዝቡ እርካታ አንጻር የተከናወኑ ስራዎች በሰፊው ለመገምገምና ምክር ቤቱም የሚያደርገውን የድጋፍና ክትትል ስራዎች  ለማጠናከር መድረኩ አስፈልጓል ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተሰናዳው መድረኩ የክልሉ አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም፣ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አሪፍ መሐመድን ጨምሮ የክልሉ  ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንትና የምክር ቤቱ አባላትና ሌሎችም ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም