ቀጥታ፡

ህዝቡ ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት- ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ 

ቦንጋ ፤ሚያዚያ 16/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።

የሕዳሴው ግድብ ክልል አቀፍ ህዝባዊ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት ለሆነው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የተጀመረው ድጋፍ መጠናከር አለበት።

የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄዱ የህዝብ ተሳትፎ ንቅናቄዎች ህብረተሰቡ በአይነትና በገንዘብ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።

የሕዳሴው ግድብ አንድነትን አስተሳስሮ መስራት ከተቻለ ለስኬት መብቃት እንደሚቻል ያስተምራል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ፣ የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ሲያደርገው የቆየውን ድጋፍ በቀጣይም ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

ግድቡ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ ያደረገና በዲፕሎማሲም ትልቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመው፣ ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ለበርካታ ዜጎች ብርሃን እንደሚሆን ተናግረዋል።

የዛሬው የንቅናቄ መድረክ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ አመራሩና መላው ህብረተሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ክልል አቀፍ የህዝብ ተሳትፎ የንቅናቄ ሰነድ በክልሉ የሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አክሊሉ ወልደሚካኤል ቀርቧል።

በሰነዱ በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የህዝብ ተሳትፎን በማሳደግ በቀጣይ ሦስት ወራት 96 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

"የሕዳሴው ግድብ ከአድዋ ቀጥሎ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ የጋራ ድልና ታሪክ ነው" ያሉት ደግሞ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ናቸው።

በቀጣይ የዞኑን ህዝብ በማነቃነቅ ድጋፉን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸው፣

ግድቡ ህዝቡ ካለው ላይ ቀንሶ ለውጤት ያበቃው የጋራ ሀብታችን ነው ያሉት ደግሞ የካፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ናቸው።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ በህዝብ ተሳትፎ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

በክልል አቀፍ ህዝባዊ የንቅናቄ መድረኩ አመራሮች ቦንድ በመግዛት ንቅናቄውን በግንባር ቀደምነት አስጀምረዋል።

በቀጣይም ንቅናቄውን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመቀጠል ዕቅዱን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተመላክቷል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ገድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ሀይል እያመነጨ ሲሆን የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በ13 ተርባይኖች 5ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሀይል እንደሚያመነጭ የሚታወቅ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም