በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ጥራትና ዘመናዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው

179

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት፣ ዘመናዊነትንና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ሲል የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2016 በጀት ዓመት የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት የፌዴራል ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን  ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝቶ የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሮባ፤ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ በመስጠትና በቁጥጥር ሥራ ያከናወናቸውን ተግባራት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በ2012 ዓ.ም ሥራ በመጀመር የቴሌኮም ዘርፍ ሪፎርሙን ለማሳካት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልፀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ አዲስ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ (ሳፋሪኮም) ገብቶ እንዲሰራ በተደረገው መሠረት የቴሌኮም ዘርፍ በውድድር እንዲሰጥ መሠረት መጣሉን አንስተዋል።

ክትትልና ቁጥጥርን ለማጠናከር ከ18 በላይ የሕግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሥራ ላይ ማዋሉን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ሁሉን አቀፍ የኢንተርኔት ተደራሽነት ክፍተት ጥናት በማድረግና ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራትን ተናግረዋል።

ከ28 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎችን ብቃት በማረጋገጥ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቃድ መስጠቱንም ጨምረዋል።

በተለይም የአገልግሎት ጥራትን በመቆጣጠር በኩል በዳታ አገልግሎት፣ በአጭር መልዕክትና በሞባይል ድምፅ በአንድ ጊዜ እስከ ሦስት አገልግሎት ሰጪዎችን ኔትወርክ መለካት የሚያስችል መሳሪያ መኖሩን ጠቅሰዋል።

የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ አለመሟላት፣ በአቅም ግንባታና ሌሎች ተቋሙ ሥራዎቹን ለማከናወን ተግዳሮቶች እንደሆኑም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የኮሚቴው የኮሙኒኬሽን ሱፐርቪዥን ቡድን አስተባባሪ ገብሬ አላምኔ፤ ባለሥልጣኑ የአገሪቱን የቴሌኮም ሥርዓት ከመቆጣጠር ውድድርና ጥራትን ለማረጋገጥ የተገበራቸው ሥራዎች  አበረታች መሆናቸውን በሱፐርቪዥን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።


 

ከተደራሽነት፣ በሰው ኃይል ማብቃት፣ ለቁጥጥርና ክትትል ሥራ የሚያግዙ መሠረተ-ልማቶችና ዘመናዊ አሠራሮችን መዘርጋቱን መገንዘባቸውን ጨምረዋል። 

ተቋሙ በአገልግሎት ጥራት፣ እራሱን በማስተዋወቅና በሌሎች ጉዳዮች ከሱፐርቪዥን ቡድኑ የተሰጡትን አስተያየቶች በመተግበር ጠንካራ ተቆጣጣሪ ለመሆን እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን በማሳካት ሂደት ጠንካራ አሠራር ለመዘርጋት በሲምካርድ ምዝገባ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

በሱፐርቪዥን ወቅት በተቋሙ ሥራዎችን ለማከናወን የተነሱ ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም