የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ከተማነት የሚመጥን የሰላምና ጸጥታ ስራዎች እየተሰሩ ነው

114

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ ነዋሪውን ያሳተፈና የዲፕሎማሲ ከተማነቷን የሚመጥን የሰላምና ጸጥታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ጌታሁን አበራ አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት የሚገኙባት የዲፕሎማቲክ ማዕከል በመሆኗ ከልማት ባለፈ ሰላምና ጸጥታዋን አስተማማኝ የማድረግ ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሰላምን ማስጠበቅ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ነዋሪውን በማሳተፍ እየተከናወኑ የሚገኙ  ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማነቷን የሚመጥኑ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ስራ ላይ መሰማራቱን ገልጸው የጸጥታ መዋቅሩ በበኩሉ ስምሪት በሚሰጠው ቦታ ላይ በንቃት እየሰራ ነው ብለዋል።

በከተማዋ የሚከበሩ የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር የሚከበሩት ህብረተሰቡ ፣ተቋማትና በየደረጃው ያሉ የጸጥታ መዋቅር በከፍተኛ ቅንጅት በመስራታቸው ነው ብለዋል።

የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ አደረጃጀቶችና ጠንካራ የመረጃ ስርዓት መፈጠሩንም አንስተዋል።

ለወንጀል ድርጊቶች መነሻ የሆኑ ቦታዎችን በመረጃ ላይ ተመስርቶ በመለየት ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውስጥና በውጭ ያሉ የተለያዩ ሃይሎች በአዲስ አበባ ላይ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ችግር ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ ከህዝብ ጋር ተቀናጅቶ በሚሰራው ስራ በከተማዋ በተለያዩ ጊዜያት ሊፈጠሩ የነበሩ የወንጀል ድርጊቶችን ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል።

የሰላምና ጸጥታን ጉዳይ ህዝባዊ የማድረጉ ስራ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም