አቅሞችንና ሀብቶችን አቀናጅቶ በመጠቀም ትልቅ የልማት ጉልበት ለመገንባት የመንግስታትን ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ነው

152

አዳማ፣ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፡-የተለያዩ አቅሞችና ሀብቶችን አንድ ላይ አቀናጅቶ በመጠቀም ትልቅ የልማት ጉልበት ለመገንባት የመንግስታት ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ ገለጹ።

የደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የመንግስታት ግንኙነት የጋራ ፎረም ምስረታ የውይይት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚሁ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክልሎች የጋራ ችግሮቻቸውን ተወያይተው በጋራ እንዲፈቱ ለማስቻል ግንኙነታቸው መጠናከር አለበት።

ግንኙነታቸው ሲጠናከር ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ የመነጋገርና የመደራደር ልምዳቸው የሚጎለብትበት አሰራር እንዲያመቻቹ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ችግሮቸውን ተነጋግረው ከመፍታት በተጓዳኝ የጋራ የመልካም አስተዳደርና ልማት አጠናክረው ለማስቀጠል እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የመንግስታት ግንኙነት ፎረም መመስረት ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር የጋራ ፍላጎቶችን ከማሳካት አልፎ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱን  እና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤የሰላም ሚኒስቴርም ከፌዴሬሽን ምክርቤትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። 


 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ በበኩላቸው ፤ ከተናጥል ጥረቶች ይልቅ የጋራ አቅሞችን በተገቢው መልኩ አቀናጅቶና አዋህዶ መጠቀም ዘርፈ ብዙ የልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶችን እንደሚያጎናጽፍ ገልጸዋል።

የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታትና የጋራ ልማትን ለማፋጠን የክልል መንግስታት ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ረገድ አዋጆችና የህግ ማዕቀፎች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።

ህጎቹን ወደ መሬት ለማውረድ ደግሞ መሰል የፎረሞች ምስረታ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

መድረኩ የአጎራባች ክልሎች የመንግሥታት ግንኙነት የፎረም ምስረታ እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አክለዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሳዓዳ አብዱረህማን እንዳሉት፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና የመንግስታት ግንኙነትን ለማጠናከር ፎረሙ ወሳኝ ነው።

በተለይም የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ሌሎች አለመግባባቶችን በጋራ ለመፍታት ፎረሙ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በመድረኩ ከኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የተውጣጡ አፈ ጉባኤዎችና ምክትል አፈ ጉባኤዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም