ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር ያላትን ወዳጅነት በንግድና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው - አምባሳደር እጸገነት በዛብህ

120

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት በንግድና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እጸገነት በዛብህ ተናገሩ፡፡

በኡጋንዳ፣ ቡርንዲ፣ ሲሸልስ፣ ኮሞሮስና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እጸገነት በዛብህ፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1964 በኡጋንዳ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በይፋ መጀመሩን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ይህን ተከትሎም በሁለቱ አገራት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩን ጠቅሰው፤ አገራቱ በተለይ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም  በፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ትብብር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የኡጋንዳ የትምህርት ጉዳዮች ልዑክ ኢትዮጵያ በዘርፍ እያከናወነች ካለው ስራ ልምድ ለመቅሰም መምጣቱን አስታውሰው፤ ይህም የአገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን አመላከች ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በኡጋንዳ እንደሚኖሩና የሁለቱ አገራት ህዝቦችም በርካታ የሚጋሯቸው እሴቶች እንዳሏቸው አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ኡጋንዳ ቀን በማዘጋጀት የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከርም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ባሻገር በንግድ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ረገድ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከኡጋንዳ በተጨማሪ ቡርንዲ፣ ሲሸልስ፣ ኮሞሮስና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መሰል ስራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበለጥ  ለማጠናከር እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም