ኢዜአ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

139

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበኩሉን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለፁ።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እና የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

ኢዜአ ለሀገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጭ ሆኖ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ባለውለታ ተቋም እንደሆነ ገልጸው፤ በጉብኝታቸው ኢዜአ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አደረጃጃት መፍጠሩን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ ተደራሽነቱን በማስፋት ለመንግሥት፣ ለግልና ለዲጂታል መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጭ በመሆን የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ረገድ አቅምና ደረጃውን እያሳደገ መምጣቱን እንደተረዱም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ ተደራሽነቱን በማስፋት መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ትልቅ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብዙ መለኪያዎች ትልቅ የመረጃ አመንጪ ሀገር እንደሆነች ጠቅሰው፤ ይህን መረጃ አደራጅቶና አጠናቅሮ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማድረስ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ያለውን ሚና አንስተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ባገናዘበ አግባብ በበርካታ የውጭ ቋንቋዎች የመረጃ ተደራሽነትን በማስፋት በቀጣናው፣ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢዜአ የዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጭነቱን ለማስፋት ከቀጣናዊና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋር ትብብርና አጋርነትን ለማስፋት የጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።

ኢዜአ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽነትና አጋርነትን ለማስፋት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ነው።

ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች ራሱን እያደራጀ የሚገኘው ኢዜአ በሀገር ውስጥ 38 ቅርንጫፎች፣ በስምንት ቋንቋዎች እና በተለያዩ አማራጮች መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ ነው።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተደራሽነቱን ለማስፋትም ከዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት ጋር የትብብር አድማሱን እያሰፋ ሲሆን በቀጣናው አገራትም ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም