የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሀገርን ከተለዋዋጭ የሳይበር ጥቃት መመከት የሚያስችል አቅም ገንብቷል-የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን - ኢዜአ አማርኛ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሀገርን ከተለዋዋጭ የሳይበር ጥቃት መመከት የሚያስችል አቅም ገንብቷል-የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016 (ኢዜአ)፦የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ተለዋዋጭ የሆኑ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት በመመከት የሀገርን ጥቅም ማስከበር የሚያስችል የተሟላ አቅም መፍጠሩን የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2016 በጀት ዓመት የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት የፌዴራል ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝቶ የመስክ ምልከታ አድርጓል።
የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በመሰረተ ልማት፣ በተቋም አደረጃጀት፣ ተተኪ የሰው ኃይልን በማፍራትና ሌሎች ተቋሙ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን ለሱፐርቪዥን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተባባሪ ዘሪሁን ከበደ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አቅም እየገነባች መሆኑን በመስክ ምልከታው እንደተረዱ ገልጸዋል።
በተለይም ተለዋዋጭ የሆነውን የሳይበር ጥቃት መመከት የሚያስችሉ፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች በመዘርጋትና በሰው ኃይል ዘርፍ የተሰሩ ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን አንስተዋል።
በተመሳሳይ በስታርት አፕ እንዲሁም የሳይበርና ቴክኖሎጂ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች ላይ እየተሰራ ያለው ተግባር ለቀጣይ ሀገራዊ ግብ መሳካት መሰረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
አስተዳደሩ በቀጣይም ያሉትን ጥንካሬዎች በማስቀጠል ክፍተቶችን እያረመ ሀገራዊ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳሬክተር ትግስት ሃሚድ በበኩላቸው የሳይበር ጥቃት ሳይፈጸም የመከላከልና ጥቃት ሲያጋጥም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።
የቁልፍ ተቋማትን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ የማልማት፣ የስጋት ዳሰሳ መስራትና ሌሎች የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል።
እንደዋና ዳሬክተሯ ገለጻ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ቁልፍ በሆኑ ተቋማት ላይ 24 ሰዓት የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣን ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ስራ የሁሉንም ተቋማት ጥረትና የህብረተሰቡን የሳይበር ግንዛቤ ማሳደግ የሚፈልግ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳሬክተር ዳንኤል ጉታ እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ምህዳሩ የሚያስተናግደው የጥቃት ዓይነትና መጠን እየጨመረ መጥቷል።
ኢትዮጵያም ይህንን ታሳቢ በማድረግ የሳይበር ጥቃትን በአግባቡ ለመመከት በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል አስፈላጊውን አደረጃጀት በመገንባት የሁልጊዜም ዝግጁነት መፍጠሩን ገልጸዋል።
የፌደራል ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን በተመረጡና ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች የሚያደርገው የመስክ ምልክታ እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡