የኢትዮጵያና ሩሲያ የባለሙያዎች ቡድን የብሪክስ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሩሲያ የባለሙያዎች ቡድን የብሪክስ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የጥናትና ምርምር ተቋማት የባለሙያዎች ቡድን በብሪክስ ማዕቀፍ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣ ከሁለቱ ሀገራት የጥናትና ምርምር ተቋማት የተወከሉ ምሁራን እና ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ሙያተኞች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በተዘጋጀው የኢትዮ-ሩሲያ የብሪክስ የባለሙያዎች ፎረም ላይ የብሪክስ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ በአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ፣ በግብርና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።
በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ፥ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የብሪክስ አባልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።
የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካ የትብብር ጥምረት የነበረው ብሪክስ አሁን ላይ አባል ሀገራቱ 10 ደርሰዋል።