በአማራ ክልል የምርጥ ዘር  አቅርቦት ችግር ለመፍታት  ርብርብ ያስፈልጋል

99

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ  16/2016(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል  የምርጥ ዘር  አቅርቦት ችግርን ለመፍታት  ርብርብ እንደሚያስፈልግ  ተመለከተ።

በክልሉ ግብርና  ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቀኛዝማች መስፍን እንደገለጹት፤  የምርጥ ዘር አቅርቦት ክፍተቶች ለክልሉ የሰብል ምርታማነት እድገት እንቅፋት ሆኗል።

ከክፍተቶቹም ለምርጥ ዘር ብዜት የሚውል መሬትና ለአባዥ ድርጅቶች የብድር አቅርቦቶት ያለመኖርን ጠቅሰዋል።

ችግሩን በመፍታት የሰብል ምርታማነትን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በመጪው የመኸር ወቅት ተገቢውን ግብዓት በትብብር በማቅረብ የአርሶ አደሩን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለዚህም ቢሮው የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንደሚወጣ የገለጹት አቶ ቀኛዝማች ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


 

"የዘር አቅርቦት ችግርን ለማቃለል ጥረት ቢደረግም የዘር ማባዣ መሬት ባለመኖሩ ተግዳሮት ፈጥሯል" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እርቄ ገላው ናቸው።

የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ዘርን በበቂና በጥራት ማቅረብ አንዱና ዋነኛው ተግባር መሆኑን ጠቅሰው የሰብሎችን ዘር በስፋትና በጥራት ለማልማት የመሬት አቅርቦት መመቻቸት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።


 

በክልሉ መሬት ቢሮ  የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ በበኩላቸው የምርጥ ዘር ማባዥ የመሬት አቅርቦት ክፍተት ለማስተካከል  በርዕሰ መስተዳደሩ የሚመራ ቦርድ ተቋቁሞ 23 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ  መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ቀደም ሲል ለባለሃብቶች ተላልፈው የነበሩና በታቀደላቸው ጊዜ ወደ ልማት ያልገባ መሬት በመንጠቅ ለምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች እንዲተላለፉ መወሰኑን ጠቅሰው በዚህም ከአንድ ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬትን ለምርጥ ዘር ማባዣነት እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።

በአማራ ክልል ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም