የአካባቢያቸውን ሰላም  በማስጠበቅ ልማትን ለማፋጠን የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የደብረብርሀን ከተማ ወጣቶች  አስታወቁ

84

ደብረ ብርሀን፤ ሚያዝያ 15/2016 (ኢዜአ)፦ የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ  የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረ ብርሀን ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

በከተማዋ ወቅታዊ ሰላምና ልማት በሚጠናከርበት ዙሪያ የሚመክር የወጣቶች መድረክ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።


 

የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ትዕግስት ፍቅረ እንዳለችው ለአካባቢ ሰላም መጠበቅና ልማት መጠናከር የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ነው።

''እኛ ወጣቶች ገንቢና ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን በማጎልበት በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ዳር እንዲደርሱ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን'' ስትል ገልጻለች።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁማለች።

አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሳለች።


 

ከወጣቶች ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ምክንያታዊ አስተሳሰብ በማስቀደም የአካባቢ ሰላም አስጠብቆ በዘላቂነት ለማስቀጠል የበኩሉን እንደሚወጣ የገለጸው ደግሞ ሌላው ወጣት ደምሴ ምሳወይ ነው።

በከተማው እያደገ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፍ መሆኑን አስታውቋል።

የእምየ ምሊኒክ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰራዊት በዛ በበኩላቸው የከተማዋን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ወጣቶች በሚያከናውኗቸው ስራዎች አበረታች ለውጥ እየመጣ ነው ብለዋል።

ወጣቶች ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ስራዎች ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ በማድረግ የጎላ ሚና መወጣታቸውን አመልክተዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የወጣቶች ዘርፍ አማካሪ አቶ ኃይለማሪያም ወንድም እሸት የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ከ9 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ አድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የወጣቶችን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተው ወጣቶች ለአካባቢያቸው ሰላም በጋራ መስራትን መቀጠል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምክክር መድረኩ ከደብረብርሃን የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶችና በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም