የከተማውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ተሳትፎአቸውን እንደሚያጠናክሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

86

ጎንደር ፤ ሚያዚያ 15 /2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በብሎክ አደረጃጀት ታቅፈው የአካባቢአቸውን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በከተማው የሰፈነውን ሰላም አጠናክሮ በማስቀጠል ዙሪያ የከተማው አስተዳደሩ ከህዝቡ የተወከሉ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ምክክር አድርጓል፡፡

ከተሳታፊዎቹ  መካከል  አቶ መስፍን ጌታነህ እንዳመለከቱት  የብሎክ አደረጃጀቱ ነዋሪው አካባቢውን ከወንጀል ፈጻሚዎች ነቅቶ በመጠበቅ ሰላሙን እንዲያረጋግጥ አግዟል፡፡

የብሎክ አደረጃጀቱ "በመኖሪያ አካባቢያችን ይፈጸሙ የነበሩ ስርቆትና የመሰረተ ልማት ዝርፊያዎችን ማስቀረት አስችሏል" ብለዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ዘውዱ መንግስቴ በበኩላቸው የብሎክ አደረጃጀቱ በባጃጅ ይፈጸሙ የነበሩ ስርቆቶች መቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ተደራጅተው በሚያከናውኑት ጥበቃ "ከዚህ በፊት ይፈጸሙ የነበሩ የንግድ ቤቶች ዝርፊያና የሰው እገታ ወንጀሎች እየቀነሱ መጥቷል" ያሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ገብሬ ዳኘው ናቸው፡፡ 

የብሎክ አደረጃጀቱ ህዝቡ ከመንግስት የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ለከተማው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እያገዘ በመሆኑም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። 


 

የአዘዞ ክፍለ ከተማ አመራር አባል አቶ ሙሉጌታ አወቀ በበኩላቸው ህዝቡ በብሎክ ተደራጅቶ ባደረገው ተሳትፎ ሁለት የኤሌትሪክ ትራንስፎርመሮችን ከዝርፊያ በማዳንና ወንጀለኞችን በመያዝ ለህግ ማቅረብ  መቻሉ ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የከንቲባው የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ቻላቸው ዳኘው የከተማው ነዋሪዎች በ91 ቀጣናዎችና በ633 ብሎኮች ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላም እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

መንግስት ሰላሙን ለማጽናት እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ በኩል የህዝቡ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ "ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከተማ አስተዳደሩ እየደገፈ ይገኛል" ብለዋል፡፡ 

የአማራ ክልል ስራ አመራር አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰብስበው አጥቃው በበኩላቸው የከተማው ህዝብ የሰላሙ ባለቤት በመሆን እያደረገ ያለው ተሳትፎ ለሌሎች አካባቢዎች አርአያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ በከተማው ከሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የአመራራ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም