በኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው 

58

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው ሲሉ የደቡብ ሱዳን የሥርዓተ ጾታ፣ የሕፃናት እና የማህበራዊ ደህንነት ሚኒስትር አያ ዋሪሌይ ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን የሥርዓተ-ፆታ እና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ልኡካን ቡድን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ  የሴቶች ኮከስ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል።

በልምድ ልውውጥ መድረኩም በኢትዮጵያ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች ኮከስ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን የሚመለከት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የደቡብ ሱዳን የሥርዓተ ጾታ፣ የሕፃናት እና የማህበራዊ ደህንነት ሚኒስትር አያ ዋሪሌይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን ሚና እየተወጣች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ደቡብ ሱዳናውያን ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው እንደሚቆጥሯት ተናግረዋል፡፡

የልዑክ ቡድኑ ጉብኝት በኢትዮጵያ ሴቶች በተለይ በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ልምድ ለመውሰድ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱና ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ደቡብ ሱዳንም ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ሴቶችን ለማብቃት የሚያስችል ልዩ ድጋፍ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ኪሚያ ጁንዲ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የሴቶችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እያሰራቸው ያሉ ስራዎችን በሚመለከት ለልዑክ ቡድኑ ገለጻ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች ኮከስ  ህጎች ሲወጡ እንዲሁም የአስፈጻሚ አካላት የክትትልና  ቁጥጥር ስራዎች ሲከናወኑ የሴቶችን ተሳትፎ እንዲጎለብት በትኩረት እንደሚሰራም አውስተዋል፡፡

የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደ ሀገር በተሰራው ስራም በምክር ቤት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም  ጨምረው ተናግርዋል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምክር ቤት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እያከናወነች ካለው ስራ ባሻገር  በዲፕሎማሲያዊ  በሰላም ጉዳዮች ያላትን ተሞክሮ ለልዑክ ቡድኑ ገለጻ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም