በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በጋራ መደገፍ ይገባል - ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ

151

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በጋራ መደገፍ ይገባል ሲሉ የመላው አፋር ህዝብ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለመጠቀም የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ በሰላማዊ አማራጭ በጋራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የእውቁ ሱልጣን አሊሚራህ ልጅ የሆኑት 15ኛው የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ከውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።

አዲስ አበባ ሲደርሱም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።


 

ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማትና ኢንቨስስትመንት እንቅስቃሴዎችን ከዳር ለማድረስ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል።

ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም ዘብ እንዲቆሙና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።

በአፋር ክልል በሰብል ልማት ረገድ የመጣውን እምርታ ጨምሮ በለውጡ መንግስት በሁሉም መስኮች ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን እያከናወኑ ያሉትን ስራ እንደሚደግፉም ነው የገለጹት፡፡

ከአፍሪካ ነጻነት በኋላም በበርካታ አፍሪካ አገራት የቅኝ ግዛት ድንበሮች እንዲቀጥሉ መደረጉን አስታውሰው፣ ይህም ኢትዮጵያን የባህር በር እንዳሳጣት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ቁጥርና እያሰመዘገበች ካለው እድገት አንጻር የባህር በር የመጠቀም ጥያቄዋ ተገቢ መሆኑን አንስተው፤ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንደሚሻም ተናግረዋል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ በበኩላቸው ሱልጣን አህመድ የመላው የአፋር ህዝብ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪ መሆናቸውን ገልጸው በልጅነታቸው ጀምሮ የታገሉለት የአፋርን ህዝብ ነጻነትና ልማት እውን ማድረግ የሚያስችል ስርዓት በመገንባቱም ከመንግስት ጎን ቆመው ትልቅ ቁም ነገር ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት መስፈን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጎን በመሆን የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ ሱልጣኑ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ የፌዴራልና የክልል መንግስታትን በሰላምና ልማት ስራዎች ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ሱልጣን አህመድን ከመሰሉ የህዝብ ባህላዊና ኃይማኖታዊ መሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ የመላው አፋር ሱልጣን የነበሩት ወንድማቸው ሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ ማረፋቸውን ተከትሎ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መሾማቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም