በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተያዘው የበልግ አዝመራ ከ251 ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ በዘር ተሸፍኗል

124

ቦንጋ ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቢሮው ምክትል ሀላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ እንደገለጹት፣ በልግ የክልሉ ዋነኛ የአዝመራ ወቅት ነው።

በዘንድሮ የበልግ አዝመራ በአዝርዕት ሰብሎች 321ሺህ 829 ሄክታር ማሳ በማልማት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል።

ከዚህ ውስጥ በእስካሁኑ ሂደት ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

አቶ አሸናፊ እንዳሉት በዘር ከተሸፈነው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ 13ሺህ 200 ሄክታሩ በትራክተር የታረሰ ሲሆን ከ85ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት ደግሞ በ1 ሺህ 600 ክላስተሮች የለማ ነው።

በክልሉ በሰፊው እየለሙ ካሉ ሰብሎች መካከል በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ሩዝ፣ ማሽላ እና ሰሊጥ ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከአምናው የተሻለ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲሁም ምቹ የአየር ጸባይ እንዳለ ገልጸው፣ ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

አቶ አሸናፊ እንዳሉት ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

እስካሁንም ቀደም ሲል የነበረን ጨምሮ 140 ሺ  ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ከ9 ሺህ 271 ኩንታል በላይ የበቆሎና የቦሎቄ ምርጥ ዘር የተሰራጨ ሲሆን አርሶ አደሮች የተሻሉ እና ነባር ዘሮችን እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ መሠራቱንም አንስተዋል።

በበልግ ወቅት በለማው የበቆሎ ማሳ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ተምች መከሰቱን እንደተግዳሮት ጠቅሰው፣ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባባር ተምቹ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ለ6ቱም ዞኖች ኬሚካል መሰራጨቱን ተናግረዋል።

የታቀደውን ምርት ለማግኘት አርሶ አደሩ የማሳ አሰሳና ቁጥጥር ሥራውን እንዲያጠናክር እንዲሁም ዩሪያን በአግባቡ እንዲጠቀም ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

የልማት ጣቢያ ባለሙያዎችና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻዎች ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።


 

በክልሉ ካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ የጡላ ቀበሌ አርሶ አደር መላኩ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው እንዳሉት በዘንድሮ የበልግ አዝመራ በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎ እያለሙ ነው።

አስፈላጊውን የግብርና ግብአት ከመጠቀም ባለፈ ለሰብላቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት ሰብሉ በጥሩ ቁመናው ላይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር ጌታቸው ወርቁ፣ ሶስት ጥማድ መሬት ላይ በቆሎ ያለሙ ሲሆን ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱና በጠየቁት መጠን ስለቀረበላቸው ሰብላቸው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ተምች በአዝመራው ላይ ጥቃት እንዳያደርስ የቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም በእጃቸው እየለቀሙ የመከላከል ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ተምቹ ብዙም ጉዳት እያደረሰ እንዳልሆነ ጠቁመው ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ኬሚካል በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብላቸው ጠየቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም