በአዳማ ከተማ በማህበር ለተደራጁ ዜጎች የምርት መሸጫ ቦታ የሚሆን ስድስት የገበያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል

68

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ በማህበር ለተደራጁ ዜጎች የምርት መሸጫ ቦታ የሚሆን ስድስት የገበያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ ገለጹ።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ በተለያየ መስኮች የስራ ዕድል በተፈጠረላቸው ዜጎች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተመልክተዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ፤ በዚሁ ጊዜ በሰጡት መግለጫ በከተማዋ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነትም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ፈጠራን ማበረታታትና ማጎልበት፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከር እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚሉ አራት ግቦች ተይዘው ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን ወጣቶች ወደ ስራ ከመሰማራታቸው በፊት ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ84 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ከ1 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ ሼዶች ተገንብተው ለወጣቶች መተላለፋቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ እጥረትን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በከተማዋ ለመገንባት ከታቀዱ አስር የገበያ ማዕከላት መካከል ስድስቱ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በማህበር የተደራጁ ዜጎች የገበያውን ሁኔታ በማረጋጋት በኩል ከፍ ያለ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም