ለስታርትአፕ የተሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት እድል የሚፈጥር ነው

113

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፡- ለስታርትአፕ የተሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት እድል እንደሚፈጥር ስታርትአፖች ገለፁ። 

በሳይንስ ሙዚየም በመታየት ላይ የሚገኘው የስታርትአፕ ኢትዮጵያ አውደ-ርዕይ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችን ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታ መሆኑን የተለያዩ ሰዎች አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል፡፡

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ዕይታ ክፍት በተደረገው አውደ-ርዕይ በመጀመሪያ ደረጃ በምርት ሙከራና ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ ስታርት አፖች እየተሳፉበት ይገኛሉ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ስታርት አፖች ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። 


 

ከነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ያብቃሉ አሰፋ እናቶች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ባሉበት ቦታ ሆነው ጤንነታቸውን የሚከታተሉበት ቴክኖሎጂ ማበልፀጉን ተናግሯል።

ለስታርትአፕ የተሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎችን በቀላሉ በማስተዋወቅ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት አጋዥ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ለመደገፍና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የራሱን ሚና እንዲወጣ ያስችላል ሲል ጠቁሟል።


 

 በስታርት አፕ አውደ ርዕይ ፈጠራውን ያቀረበው ቃለአብ ግርማ በበኩሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ድጋፍ ከሚሹ ወገኖች ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማበልፀጉን ገልጿል።

ቴክኖሎጂው የመረዳዳትና የመደጋገፍ  ባህልን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግሯል።


 

ምርቶችን ለህብረተሰቡ በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችል ኢ-ኮሜርስና ሎጀስቲክን ያካተተ ቴክኖሎጂ  መስራቱን የተናገረው ደግሞ በረከት ታደሰ የተባለ የፈጠራ ባለሙያ ነው ።

መንግስት ለስታርት አፕ ትኩረት በመስጠት ፖሊሲዎችን በማዘጋጀትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግሯል።


 

በሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ድጋፍ ባለሙያ አቶ ነገደ ይስሃቅ ስታርት አፖች ፈጠራ ስራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸውን መሆኑን አስታውቀዋል።

ስታርት አፖች ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም