በከተማው የተገነቡ ፓርኮች ምቹና አማራጭ የመዝናኛ ሥፍራዎች ሆነዋል

86

አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 15/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ፓርኮች ለከተማዋ ውበት ከመሆን ባለፈ ለቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራዎች መሆናቸውን የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በጥቂት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ፓርኮች ከቱሪስት መዳረሻነትም ባለፈ የከተማዋ የውበት መገለጫ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።


 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የአንድነት፣ የእንጦጦ እና ሸገር ፓርኮች እንዲሁም የወዳጅነት አደባባይ ለዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ጎብኝዎች ፓርኮቹ የአዲስ አበባን ገፅታ ያስዋቡና ለመዝናኛነት የምንመርጣቸው ዓይነተኛ ሥፍራዎች ሆነዋል ብለዋል።


 

ፓርኮቹን ሲጎበኙ ካገኘናቸው መካከል አቶ ማንደፍሮ አሰፋ እና ወይዘሮ ሰላማዊት ሙሉጌታ በተለይ አንድነት ፓርክ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መስህቦቹ በአንድ ላይ በመያዙ  በርካታ ነገሮች ማየት ያስችላል ብለዋል።

በተለይ ለትራንስፖርት አመቺ በሆነ ሥፍራ መገንባቱ ብዙ ድካም ሳይኖር በቀላሉ ተዝናንቶ ለመመለስ ጥሩ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በአዲስ አበባም ሆነ በአገሪቱ እየተሰሩ ያሉት ፓርኮች የአገሪቱን ቱሪዝም በማነቃቃትና ሰዎችም ምቹ የመዝናኛ ሥፍራ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፓርኮቹ በቂ የመኪና ማቆሚያና ከከተማው ያልራቁ በመሆኑ በቅርበት እንዲዝናኑና በቀላሉ መንፈሳቸውን ለማደስ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

በተለይ በአዲስ አበባ መሃል እንዲህ ዓይነት ፓርኮች መሰራታቸው በሥራ ጫና የደከመ አእምሮን   ዘና ለማድረግ ጥሩ  አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ወይዘሮ ቃልኪዳን ኃይለማሪያም፣ ወይዘሪት ስምረት ፍስሐ እና አቶ ንጉሴ ለማ ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች እምቅ ኃብቶችንና እሴቶችን እየተመለከቱ መዝናናት መቻል ትልቅ ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በዚህም ከተጣበበ ጊዜ የተነሳ ለመዝናናት ላልቻሉ ዜጎች ጥሩ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው በፓርኩ ህጻናት ልጆችን ይዘው በአነስተኛ ዋጋ መዝናናት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።


 

ከወላጆቻቸው ጋር ለመዝናናት የመጡ ህፃናት በበኩላቸው፤ በፓርኮቹ ባዩት ነገሮች መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የአንድነት ፓርክ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ጌታቸው በየነ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ፓርኩ በቀን በርካታ ጎብኝዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ፓርኮቹ የጉብኝት ባህል እንዲያድግና የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጉብኝዎች ቁጥር እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ገልፀዋል።

በመዲናዋ የተገነቡት ፓርኮች የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጎብኝዎች ሁነኛ የመዝናኛ ሥፍራ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና ወዳጅነት አደባባይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለቱሪስቶች ክፍት የተደረጉ ውብና አስደናቂ ሥፍራዎች መሆናቸው ይታወቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም