በኦሮሚያ ክልል በካፒታል እቃ ሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት ከ5 ሺህ በላይ ማሽነሪዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ሆነ

66

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት ከ5 ሺህ በላይ ማሽነሪዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መሆናቸውን የክልሉ ካፒታል ዕቃ ንግድ አክሲዮን ፋይናንስ ማኅበር ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ በአነስተኛና መካከለኛ የተደራጁ 6 ሺህ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።

የኦሮሚያ ካፒታል እቃ ንግድ አክሲዮን ፋይናንስ ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ገለታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማኅበሩ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳለጥ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው፡፡ 

ማኅበሩ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎትና ቱሪዝም ልማት ለተሰማሩ ዜጎች  በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት የብድር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም ከዚህ በፊት የነበረውን የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ማህበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ በክልሉ በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት  ከ5 ሺህ በላይ የማሽነሪ ምርቶችን በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ወደ 339 ሚሊዬን ብር የሚገመት ሃብት ማስመዝገብ እንደቻሉ ገልጸዋል።

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ዜጎችም ኑሯቸውን ከማሻሻል ባለፈ በስራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወሾ ከድር፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የሚደረገው ድጋፍ ዘርፉ እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማትና የማምረቻ መሳሪያ ያለባቸውን ማነቆ ምላሽ ለመስጠት ከልማት ባንክና ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለተኪ ምርት የተሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የተደራጁ 6 ሺህ የሚጠጉ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንቨስትመነት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡  

የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ስራዎችም ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ በማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም