የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

81

ድሬዳዋ፤ሚያዝያ 15/2016  (ኢዜአ) ፦ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የአስተዳደሩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሴክተር ተቋማትና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ዘርፎች የስራ አፈፃጸም ሪፖርት እየተገመገመ ነው።

በዚህም በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሀብትና በመልካም አስተዳደር የተከናወኑ ስራዎች በትኩረት እየተፈተሹ መሆናቸውም ታውቋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት በገጠርና በከተማ  የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር  ስራዎች አበረታች ለውጦች እያመጡ ናቸው።

በተለይም ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት፣ ለነዋሪዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብና የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ለውጦች በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ሌት ተቀን ርብርቡን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።

በተመሳሳይ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና ከተማዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ የተከናወኑ የማህበራዊ ዘርፍ ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው በየተቋማቱ የተጀመሩ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሂደቶችን በማጠናከር የህዝብ ጥያቄዎች በፍጥነትና በጥራት የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በበጀት አመቱ 124 ነባርና አዳዲስ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያቃልሉ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የፕላንና ኢኮኖሚ  ኮሚሽን ኮሚሽነር  አቶ ኃይለማርያም ዳዲ ናቸው።

ከእነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አስራ ሁለቱ  ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ሰባቱ ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

እንደ አቶ ኃይለማሪያም ገለፃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በተከናወኑ ተግባራትም ከሦስት ቢሊዮን 234 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በማገኘት የዕቅዱ 85 በመቶ ተሳክቷል።

ከመዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች  ለማግኘት  የታሰበውን ገቢ በቀሪ ወራት ለመሰብሰብ መረባረብ እንደሚገባ በማከል።

የግምገማው መድረክ እንደቀጠለ ሲሆን የአስተዳደሩ የአመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም