መልከ ብዙው የ"ዳሞታ ተራራ"

302

 የዳሞታ ተራራ ወላይታዎች የሚታወቁበት የራሳቸው የሆነ ባህል፣ ቅርስ እንዲሁም መለያ ምልክት ነው። ዳሞታ የወላይታ የልምላሜ መገለጫና የተፈጥሮ መስህብ ነው። ተራራው በወላይታ ሶዶ ከተማ ዙሪያ በሚገኝ 12 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በ32 ምንጮችና በ12 ጅረቶች ታጅቦ በኩራት ተንሰራፍቶ የሚገኝ የአካባቢው ማህበረሰብ መጠሪያ ነው። ከዚህ የተነሳ የወላይታ ሶዶ ከተማን ተፈጥሮ ካደላት የዳሞታ ተራራ ሞገሷ የተነሳም ተራራው ፀዳሏ ነው ብለው የሚጠሩትም አልጠፉም። የዳሞታ ተራራ ለአካባቢው ነዋሪም ሆነ አካባቢውን ሊጎበኙ ለሚመጡ እንግዳ ተቀባይነቱን በአረንጓዴ የተፈጥሮ መስህቦቹ በማሸብረቅ ውበቱን በመግለፅ የሚያሳይ ተራራ ነው። ተራራውን ወደ ላይ ለሚመለከተው ዳሞታ ብዙ የሚያሳየውና የሚነግረው ታሪክ እንዳለው ያሳብቃል።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት የዳሞታ ተራራ ለ800 ዓመታት ገደማ የቆየ ታሪካዊ የመስህብ ስፍራ ነው። በጥቅጥቅ ደኖች፣ በወራጅ ወንዞችና ጅረቶች፣ ለመድኃኒትነት በሚያገለግሉ ቁጥር ስፍር በሌላቸው የእፅዋት ዘሮችም የተሸፈነ ነው። በወላይታ ዞን እምብርት በወላይታ ሶዶ ከተማ ሰሜናዊ አቅጣጫ ከፍታ ላይ የሚገኘው የዳሞታ ተራራ ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ 3000 ሜትር እንዲሁም የዙሪያ ልኬቱ ከ68 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሆነም ይነገራል።

በአንድ ወቅት ተራራው በአካባቢ መራቆት፣ በአየር ሚዛን መዛባትና በሌሎች ምክንያቶች ግርማውንና ልምላሜውን እያጣ መጣ። ይህም የወላይታን ህዝብ በማሳሰቡ ሁሉም የአካባቢው ማህበረሰብ ልጅ አዋቂ ሳይል ርብርብ በማድረግ ወደ ቀደመ አቋሙና ሙላቱ ለመመለስ ብርቱ ተፈጥሮን የመከላከል ፍልሚያ አደረገ። ፍልሚያውም በአካባቢው ማህበረሰብ አሸናፊነት በመጠናቀቁ ተራራው ልምላሜውን ጠብቆ አሁን የተላበሰውን ግርማ እንዲይዝ በማድረግ ሊያጣው የነበረውን ጥቅጥቅ ደን በመመለስ የመሬት መሸርሸርን ከመከላከልና የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ከመጠበቅ አልፎ ትልቅ የአይበገሬነት ታሪክ እንደፃፈም ይወሳል። ለዚህም ነው ዳሞታን ከወላይታዎች ማህበረሰቡን ከተራራው ለመለየት እንደማይቻልና ጠንካራ ተዛምዶን የመሰረቱ መሆናቸው የሚገለፀው።

የወላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ አብርሃም ባቾሬ እንደሚሉትም ዳሞታ በርካታ የቱሪስት መስህቦች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሀገር በቀል እፅዋት፣ የዱር እንስሳትና ጥንታዊ የወላይታ ነገስታት መናገሻ ስፍራዎች ባለቤት ነው። የዳሞታ ተራራ ከወላይታ ህዝብ ታሪክና ጀግንነት እንዲሁም ከአሸናፊነት ወኔው ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑም ያነሳሉ። በዙሪያው ዘመናትን ያስቆጠረ የጥቅጥቅ ደንና የነገስታት መኖሪያ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትና አድባራት የሚገኙበት መሆኑን አንስተው ለወላይታ ሶዶ ከተማም የተለየ ግርማ ሞገስን እንዳላበሳት ተናግረዋል።

በዳሞታ ተራራ ዙሪያ የተኮለኮሉት ወንዞችም መነሻቸውን ከተራራው በማድረግ ወደ ታች እየተገማሸሩ ይነጉዳሉ። ወይቦ፣ ቁሊያ፣ ካልቴ ቶቦቤ፣ ሀመሳ፣ ሊንታላ፣ አይከሬ፣ ዋላጫ፣ ጫራቄ፣ ቦልዖ፣ ካዎ ሻፋ፣ ጋዜና ሻፋና ሌሎች ወንዞች ከዚሁ ተራራ ተጎራብተው፣ ከተራራው ያገኙትን መዳኛ ፀበል ለሌሎች ለማቋደስ አየተንደረደሩ ይወርዳሉ። ለአካባቢው ማህበረሰብም ልምላሜያቸውን ያጋባሉ፤ ብርቱውን መሬቱን ምሶ ገበታውን እንዲያበለፅግ ያተጋሉ። ሁሉም ግን የዳሞታ መልዕክተኞች፣ የዳሞታ ተጧሪዎች ናቸው።

እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ የክርስትና ሀይማኖትን በአካባቢው በማስፋፋት ስመ ገናና የሆኑት አቡነ ተክለሃይማኖት ክርስትናን ለመስበክና መንፈሳዊ ክዋኔዎች ለመፈጸም ዳሞታ ተራራን ይወጡ እንደነበረ ከልጅነታቸው ይነገራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የመንፈሳዊ አገልግሎቶችን ሲያከናውኑ ድካም ሲሰማቸው እረፍት የሚያደርጉበት ለመንፈስ ሃሴትን የሚያጎናፅፍ ስፍራ ነው የዳሞታ ተራራ።

በዚህ ምክንያት "ጦሳ ፔንጊያ" የእግዜር መተላለፊያ የተሰኘ ስያሜ የተሰጠውና "ጣዛ ጋሯ" የንጉስ ሞቶሎሚ ቤተ-መንግስት፣ የንጉስ ሞቶሎሚ የጥምቀት ሥፍራ፣ ቆሊ ቦርኮታ፣ ዳጌቾ፣ ቦቄና ሶዶ፣ ጦማ ገሬራና ሌራቶ ጎዳ የተሰኙ ታሪካዊና የሚጎበኙ ስፍራዎች ይጎበኙበታል በዳሞታ ተራራ። ካዎ ሞቶሎሚ፣ ካዎ ዳሞቴ፣ ካዎ ጎቤና ካዎ ጦና የሚባሉ የወላይታ ነገስታት ቤተ-መንግስታቸውን በተራራው አናትና ግርጌ ላይ ይገነቡ እንደነበር አቶ አብርሃም ይናገራሉ።

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ፣ የዳሞታ ተራራ በወላይታ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለው መሆኑን ይገልፃሉ። ከተራራው አናት መነሻቸውን የሚያደርጉ ወንዞች የወላይታን ምድር አጥግበው ሰዎችና እንስሳቱን አጠጥተው ወደ ብላቴ እና ኦሞ ወንዝ ይፈሳሉ። የዳሞታ ተራራ ሌላው ጠቀሜታው መሬት እንዳይሸረሸር ቀጥ አድርጎ በዛ ግዝፈቱ ይዟል ይሄም ለመንገድ ደህንነትና የአካባቢውን አየር ተስማሚ ከማድረግ አኳያ አይተኬ ሚና አለው። በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነው የዳሞታ ተራራ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከዘመናት በፊት ተጀምሮበታል ይላሉ አስተዳዳሪው። ንፁህ የመጠጥ ውሃን በከፊል ለሶዶ ከተማ የሚያጠጣውን የዳሞታ ተራራ የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ከዩኒቨርስቲና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነውም ብለዋል።

የዳሞታ ተራራ ታሪካዊ ይዘቱን ስንመለከት አካባቢው ቀደም ሲል የነገስታት መናገሻ ቦታ ነበር የሚሉት ደግሞ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከወላይታ ሥርወ-መንግስት መካከል ካዎ ሳቴ ሞቶሎሚና የሌሎች ነገሥታት መናገሻ ስፍራ ስለነበር በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው ታሪካዊ ስፍራ ነው። የዳሞታ ተራራ ለአብዛኞቹ በወላይታ ዞን ለሚገኙ ወረዳዎች የስያሜያቸው መነሻ ነው። ዳሞት ጋሌ፣ ዳሞት ሶሬ፣ ዳሞታ ወይዴ፣ ዳሞት ፑላሳ ወረዳዎችና ሌሎች ቀበሌያት የተራራውን ስም መነሻ ያደረጉ መሆኑ ተራራውን ታሪካዊ ያደርገዋል።

እዚሁ ተራራ ላይ ካሉ የተለያዩ መስህቦች መካከል የጥንታዊ ዋሻ "ሞቼና ቦራጎ" ዋሻ አንዱ ነው። ይህ ዋሻ በወላይታ ሶዶ ከተማ በሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ የጥንት ሰው መኖሪያ ዋሻ ነበር። ዋሻው በዳሞታ ተራራ ከሚገኙ ከአምስት በላይ ዋሻዎች አንዱ ሲሆን በተራራው በስተምዕራብ አቅጣጫ በኩል የሚገኝና ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሰዎች በዚሁ ዋሻ ይኖሩ እንደነበረም ታሪክ ያስረዳል። ሞቼና ቦራጎ ዋሻ ስፋቱ  38 ሜትር፣ የጣሪያው  ከፍታ 33 ሜትር፣ የዋሻው ዙሪያ ልኬት ደግሞ  58 ሜትር፣ እንዲሁም በውስጡ ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች የመያዝ አቅም ያለው እንደሆነም መረጃዎች ያመላክታሉ።

ሌላው ከዳሞታ ተራራ መስህቦች መካከል አንዱ የሆነውን ደብረ-መንክራት አቡነ ተክለኃይማኖት ገዳም ላስተዋውቃችሁ። ይህ ገዳም ለአቡነ ተክለኃይማኖት መታሰቢያነት በ1887 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ ከመመስረቱ ጋር በተያያዘ የተገነባና በዳሞታ ተራራ ምዕራባዊ ራስጌ የሚገኝ የቱሪስት መስህብ ሥፍራ እንደሆነ ነው ዶክተር አበሻ የሚናገሩት።

ገዳሙ የአምልኮና የፀበል አገልግሎት እየሰጠ ከአንድ ክፈለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ በወላይታ ዞን ካሉ መንፈሳዊ ስፍራዎች አንዱ ሲሆን በውስጡ በርካታ ሐይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ያሉት በመሆኑ በኢትዮጵያ ሐይማኖታዊ ጉዞ ከሚደረግባቸው መዳረሻዎች አንዱ ነው። በመሆኑም አካባቢው ለቱሪስት መዳረሻነት፣ ለአካባቢው ልማት ብሎም ለአየር ንብረት ሚዛንን መጠበቅ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም