የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ነው
ሮቤ ፤ ሚያዝያ 15 /2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ሁሉም በመገንዘብ ለስኬታማነቱ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ።
"የባህር መውጫና ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ዛሬ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ የባህር በርን አስመልክቶ በቀረቡ የመነሻ ጹሑፎች ያለውን ሀገራዊ ጠቀሜታና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በንጽጽር በማሳየት ተብራርቷል።
የባህር በር ተጠቃሚነትና ለቀጣናዊ ትስስርና፣ ለዘላቂ ሰላም ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ምሁራን እንዳመለከቱት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ጥያቄ ጉዳይ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ ነው።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሐመድ ጀማል ለአንድ ሀገር የባህር በር አስፈላጊነት የተመለከተ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሑፋቸውም የባህር በር ለአንድ ሀገር የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ያለው ድርሻ ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ የባህር በር "ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መደገፍ አለበት" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ተጠቅማ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር መሐመድ እንዳሉት፣ የባህር በርን ሰላማዊ በሆኑ አማራጮች ለማግኘት ለሚደረገውን ጥረት ስኬት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ድርሻ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በንግድና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ መስኮች ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠር እየሰራች መሆኗን ያነሱት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ አባተ ናቸው።
በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ የመልማትና የጋራ ብልፅግናን የማረጋገጥ ፖሊሲን እየተገበረች መሆኗን ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ መሆኑ አመልክተዋል።
ዶክተር አለማየሁ ፤ የባህር በር አጠቃቀም ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ ሳይሆን ምሁራንና በየደረጃው የሚገኙ ዜጎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሌላው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኢሳ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበልና በዲፕሎማሲ መርህ በሰላማዊ አካሄድ የባህር በር ለማግኘት ጥረት መደረጉ የሚበረታታ ነው።
የባህር በር ለሀገር ከሚሰጠው ጠቀሜታ በዘለለ ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማት ያደረገችው የትብብር ስምምነት የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
"አጀንዳው ትልቅ ሀራዊ ጥቅም የሚያመጣልን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ጉዳይን መንግስት ሲያነሳው ብቻ የምንወያይበት ሳይሆን ተቋማዊና የጋራ መሆን አለበት" ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ከራስ ጥቅም አልፎ ለቀጣናው ሀገራት ዘላቂ ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በዛብህ ወንድሙ፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በምርምር የተደገፉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰራባቸው አጀንዳዎች አንዱና ዋናው እንደሆነ አመልክተዋል።
የባህር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥያቄን ለዓለም ለማስረዳት የምታደረገውን ጥረት ምሁራን በጥናትና ምርምር በመደገፍ አጀንዳው በዜጎችና ሌሎች ሀገራት ዘንድ በቅጡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ ምሁራንን ጨምሮ ሌሎችም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።