በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው የካላዛር ህክምና መድሃኒት ወደ ምዕራፍ ሁለት ክሊኒካል ሙከራ ደረጃ ተሸጋገረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው የካላዛር ህክምና መድሃኒት ወደ ምዕራፍ ሁለት ክሊኒካል ሙከራ ደረጃ መሸጋገሩን ፈውስ ትኩረት ለተነፈጋቸው በሽታዎች ኢኒሼቲቭ  አስታወቀ።

በምርምር ላይ ያለው የካላዛር መድሃኒት በአፍ የሚወሰድ ሲሆን  በምስራቅ አፍሪካ በሽታውን ለማጥፋት የተያዘው ግብ እውን እንዲሆን ያግዛል ተብሏል።

በሳይንሳዊ ስሙ ''ቬሴራል ሊስማናሊስ'' በተለምዶ ካላዛር የሚባለው በሽታ በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 80 አገራት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሽታው በተለይም ሞቃታማ በሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይከሰታል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካላዛር በሽታ ጥናትና ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ሳሙኤል ተሾመ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የካላዛር በሽታ የመጨመር አዝማሚያ በማሳየቱ ለበሽታው ፈዋሽና አስተማማኝ መድሃኒት ለማግኘት የሚደረገው ምርምር ወደ ምዕራፍ ሁለት መሸጋገሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል። 

ምርምሩ መድሃኒት ሆኖ ለታማሚው ለመድረስ ከዚህ በኋላ ሁለት ደረጃዎችን ማለፍ እንደሚጠበቅበት ገልጸው፣ ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ ህክምና የማስገኘት እድሉ ሰፊ  መሆኑንም ተናግረዋል።

ምርምሩን ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ አገራት ተመራማሪዎችና የላቦራቶሪ ተቋማት ጋር በጋራ እያከናወኑት መሆኑንም አስረድተዋል።

በአፍሪካ አሁን ላይ የካላዛር ህክምና ለ17 ቀን በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የመድሃኒት ሙከራ ምርምር መስፈርት መሰረት እየተካሄደ ያለው አዲሱ የ“LXE408” መድሃኒት በአፍ የሚወሰድ ሲሆን መድሃኒቱ አሁን ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ህክምና አማራጮች ውስንነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ህሙማን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝና ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው መታከም ግዴታ እንደሚሆንባቸው አመልክተዋል።

በምርምር ላይ የሚገኘው ህክምና ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛ፣ ህሙማን ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ህክምናውን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የሚያግዝ እንደሚሆን ይጠበቃል ነው ያሉት። 

በአለም ጤና ድርጅት ተመራማሪና የካላዛር በሽታ መከላከል ተጠሪ ሳዉራብ ጃይን (ዶ/ር) እኤአ በ2030 ለህብረተሰብ ጤና ጠንቅ የሆኑትንና ትኩረት የተነፈጉ የትሮፒካል በሽታዎች በዋናነትም ካላዛርን ለማጥፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ አዳዲስ ምርምሮችን ማካሄድና የተሻሻሉ የህክምና ዘዴዎችን መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል።

የካላዛር በሽታ ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ፣ ከልክ ያለፈ የጣፊያና የጉበት ዕድገትን ያስከትላል።

በምስራቅ አፍሪካ በየዓመቱ ከ30 አስከ 40 ሺ ሰዎች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን አብዛኞቹ ህሙማን በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን አንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በየአመቱ ከ50 እስከ 90ሺ ሰዎች በካላዛር የሚያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ከግማሽ በላይ ናቸው ተብሏል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ክሊኒካዊ ሙከራ የገንዘብ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCPT) መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም