ስታርት አፖች በጤናው ዘርፍ ያቀረቧቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥራቱን የጠበቀና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ናቸው

71

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፦  ስታርት አፖች በጤናው ዘርፍ ያቀረቧቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥራቱን የጠበቀና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢንስቲትዩት ኦፍ ፋርማሲዩቲካል ሳይንስ መምህራን ገለፁ።

በስታርት አፕ አውደ ርዕይ የቀረቡት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የአገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ከመሰረቱ መቀየረ የሚያስችሉ በመሆኑ ተግባር ላይ እንዲዉሉ እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ምሁራኑ ተናግረዋል።

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።      

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ-ርዕዩ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል። 

አውደ ርዕዩን ሲጎበኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢንስቲትዩት ኦፍ ፋርማሲዩቲካል ሳይንስ መምህራን በቴክኖሎጂ ዘርፍ አቅም ያላቸውና ለቀጣዩ ትውልድ መነሳሳትን የሚፈጥሩ ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንስቲትዩት ኦፍ ፋርማሲዩቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ከተማ ታፈሰ እንዳሉት በወጣት ስታርት አፖች  እየተሰሩ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ዲጂታል ኢኮኖሚውን የሚደግፉና አገርን የሚያሳድጉ ናቸው።

በጉብኝታቸው በትምህርት፣በሎጅስቲክስ፣ በህክምናና በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ወደ ስራ መቀየር የሚችሉ የቴክኖለጂ ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ ለነገ መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን መመልከታቸውን የገለፁት ደግሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንስቲትዩት ኦፍ ፋርማሲዩቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ተሾመ ደግፌ  ናቸው።

በተለይ በጤናው ዘርፍ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች ስራን የሚያቀላጥፉና ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው መምህራኑ የተናገሩት።                   

የጤናው ዘርፍ  ቴክኖሎጂ ይዘው የቀረቡ ስታርት አፖች በበኩላቸው ታካሚዎች በቤታቸው ሆነው ከህክምና ቀጠሮ ጀምሮ ህክምና እስኪያገኙ ድረስ ያለውን ሂደት የሚያሳልጠው ቴክኖሎጂ እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን ገልፀዋል።

"የርህራሄ የስኳር ህክምና ማዕከል" ማርኬቲንግ ባለሙያ ዶክተር ያኔት ዕቁባይ ማዕከሉ የስኳር ህመምን የተመለከተ ትምህርትና በጤና ባለሙያዎች የቤት ለቤት እንክብካቤና ህክምና መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልፃለች።

"የጤናዎ " የኦፕሬሽን ዘርፍ ባለሙያ ፍሬህይወት ደመላሽ በበኩሏ በድረገፅ ፣ ሞባይል መተግበሪያና በጥሪ ማዕከል በመታገዝ ታካሚዎች ማንኛውንም ህክምና ማግኘት የሚችሉበትን ቴክኖሎጂ ይዘው መቅረባቸውን ተናግራለች።

"የጤና ፈርስት ፕላስ" ማርኬቲንግ ባለሙያ ሃይማኖት ታዬ እንዳለችው ቴክኖሎጂው የቴሌ ህክምና የሚሰጥበት ሲሆን ታካሚው በድምጽና ምስል ጥሪ፣ በጤና ተቋማት በመምጣት እንዲሁም የቤት ለቤት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።

ይዘው የቀረቧቸው ቴክኖሎጂዎች የታካሚን እንግልት የሚቀንሱና የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ ስራን እንዲሰሩ እድል የሚፈጥር ነው።

መሰል መድረኮች ስታርት አፖች ስራቸውን እንዲያስተዋውቁና ከሌሎች ስታርት አፖች ልምድ እንዲቀስሙ የሚያስችሏቸው እንደሆኑም ተናግረዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም