የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ የታዩ ልምዶች ይበልጥ መጎልበት ይገባቸዋል

159

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፦  የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ረገድ የታዩ ልምዶች ይበልጥ መጎልበት እንዳለባቸው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የኮርፖሬሽኑን ዋና መሥሪያ ቤት፣ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል፡፡


 

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል፤ ኮርፖሬሽኑ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁበት የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ አንጋፋ የመንግሥት ተቋም ቢሆንም ለውጡ እስከመጣበት 2010 ዓ.ም ድረስ ዕድሜውን በማይመጥን ችግር ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ ማግስት በተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ለ42 ዓመታት ከቆየበት ችግር በማውጣት ትርፋማና ተወዳዳሪ ተቋም ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሪፎርሙ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የኮርፖሬሽኑን የማስፈፀም አቅም ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ 


 

ኮርፖሬሽኑ የቤቶችን የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት፣ ለቤቶች መለያ ምልክት በመለጠፍ፣ ጂ.ፒ.ኤስ እና ወደ ጎግል ካርታ በማስገባት የኮርፖሬሽኑን የቤት አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻል መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የንግድ ቤቶችን ኪራይ በማሻሻል የገቢ አማራጮችን እያሰፋ መሆኑን ገልጸው፤ በ2010 ዓ.ም.የተቋሙ ገቢ ከነበረበት 308 ሚሊየን ብር በ2015 ዓ.ም. ወደ 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለ28 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የቤቶች ግንባታ ከማስጀመርም ባለፈ፤ የጥራት፣ ጊዜና የግንባታ ዋጋ ማሻሻል ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤ የኮርፖሬሽኑ ተቋማዊ አመራር ከዋና መሥሪያ ቤት እስከ ቅርንጫፍ ወጥነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ለማሻሻል የተጀመረው የቤቶች የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶችን በአግባቡ በመከታተል በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራት እና ዋጋ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ያለው ተግባር ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

ከቤቶች ልማት ጎን ለጎን በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የብሎኬት እና የኮንክሪት ማምረቻ ፋብሪካ የዘርፉን ችግር ከመፍታት ባለፈ ለኢንዱስትሪው ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፤ የኮርፖሬሽኑ የቤቶች ግንባታ እንደ ሀገር ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

በግንባታ ሂደት የሚሳተፉ ባለቤቶች፣ አማካሪዎችና ተቋራጮች ጥምረት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በበኩላቸው፤ የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የመስክ ምልከታ የበለጠ ለመሥራት የሚያበረታታ ነው ብለዋል።


 

የተሰጠውን አስተያየት በመቀበል ተቋሙ አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ ለመሥራት እንደሚያነሳሳም  አቶ ረሻድ ተናግረዋል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተመረጡና ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች የሚያደርገው የመስክ ምልከታ እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም