በክልሉ በዘጠና ቀን ዕቅድ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል--ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

99

ቦንጋ ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘጠና ቀን ዕቅድ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና እርካታ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ። 

የክልሉ መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው። 


 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፣ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም ትኩረት የሚፈልጉ ቀሪ ሥራዎች አሉ። 

ባለፉት ወራት በተሰሩ ሥራዎች በርካታ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው የተሻለ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በበጀት እጥረት፣ በአስተዳደር ችግሮች እና በማስፈፀም አቅም ውስንነት ምክንያት ያልተፈፀሙ ተግባራት እንዳሉ ገልጸዋል።

እነዚህን ያልተከናወኑ ተግባራት በመፈፀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና እርካታ ለማሳደግ የዘጠና ቀናት ዕቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የዘጠና ቀናት ዕቅዱ ከክልሉ መደበኛ ዕቅድ በተጨማሪ የፌደራል ሱፐርቪዢን አባላት እና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባልት በክልሉ ባደረጉት የድጋፍና ክትትል ሥራዎች የተሰጡ ግብረመልሶችን መሰራት ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ ፈጣን ምላሽ ለሚፈልጉ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠትና በተሰጠው ግብረመልስ መሰረት የማስተካከያ ስራዎችን ለመስራት የዘጠና ቀኑ እቅድ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ኢንተርፕራይዞችን በተመለከተ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን የድጋፋና ክትትል ራዎችን እየተሰሩ መሆኑንም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ተናግረዋል።

በዘጠና ቀናት ዕቅድ ውስጥ ለማከናወን የታሰቡትን ተግባራት በአግባቡ በመፈጸም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና እርካታ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል 

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም