ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2025 ተጨማሪ የካርበን ሽያጭ ማግኘት የሚያስችላትን መስፈርት አሟልታለች - የኢትዮጵያ የደን ልማት

176

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2025 ተጨማሪ የካርበን ሽያጭ ገቢ ማግኘት የሚያስችላትን መስፈርት ማሟላቷን  የኢትዮጵያ የደን ልማት አስታወቀ። 

ባለፉት አምስት አመታት ዜጎችን በማሳተፍ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች የደን ሽፋን እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል፡፡

ከመርኃ ግብሩ ጎን ለጎን የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት የደን ጭፍጨፋን በግማሽ መቀነስ መቻሉን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል ።

በኢትዮጵያ የደን ልማት የብሔራዊ ሬድ ፕላስ አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን በመሸፈን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የራሷን ድርሻ እየተወጣች ነው። 

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ከሚገኘው የደን ልማት ከካርበን ሽያጭ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የካርቦን ሽያጭ ገቢ ለማግኘት የተቀመጡ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች እንዳሉ ጠቁመው ኢትዮጵያ ከካርቦን ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችሏትን መስፈርቶች  እንዳሟላች ተናግረዋል። 

የካርበን ሽያጭ ገቢ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በአካባቢና በአየር ንብረት ሚዛናዊነት ጥበቃ ላይ የሚያበረክቱት የካርበን መጠን ተለክቶ የሚፈጸም የክፍያ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል። 

በሰው ሰራሽ የደን ሽፋን የተራቆቱ አካባቢዎችን የማልማት ተግባሩ በባለሙያና በሳተላይት መረጃ  ተንትኖ የሚቀርብ ሲሆን በዚህም ለአየር ንብረት ተጽዕኖና የካርበን ክምችት ያበረከተው አስተዋጽኦ ተለክቶ ለሽያጭ የሚቀርብ መሆኑን አንስተዋል። 

በኢትዮጵያ እየተሰራበት በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የደን ሽፋኑን ከ17 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉ ሀገሪቷ ወሳኝ የአካባቢ ጥበቃ ምዕራፍ ላይ መሆኗን እንደሚሳይ ተናግረዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2025 ከካርበን ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጸዋል። 

የካርበን ሽያጭ ለመፈጸም የሚተከሉ ችግኞችን ደን በማድረግ፣ መረጃን በዲጂታልና በጂፒኤስ በመመዝገብ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ ማቅረብ እንደሚጠይቅ አንስተዋል። 

በኢትዮጵያ የተከናወኑ የደን ልማት ተግባራትን በአግባቡ አደራጅቶ በመመዝገብ ሪፖርት ቀርቦ ባለሙያዎች በአካልና በሳተላይት ምልከታ አድርገው ተጨማሪ የካርበን ሽያጭ  ገቢ ማግኘት የሚያስችላትን መስፈርት ማሟላቷን የሚገልጽ ምላሸ እንደተሰጠ አስታውቀዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ የሚሰሩ አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከዓለም ባንክ፣ከኖርዌይና የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ እስካሁን ከካርበን ሽያጭ ከ100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን ጠቁመው፥ በሬድ ፕላስ በተደገፈው የባሌ ደን ካርበን ሽያጭ ብቻ በሁለት ዙር 12 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል። 

ከካርበን ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለህብረተሰብ ተሳትፎና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት በመስጠት ቀጣይነት ያለው የደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራ እንደሚውል ተናግረዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ዘመቻን በማስቀጠል ከደን ልማት የካርበን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የአካባቢ ጥበቃ ሙያተኞች የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግ ለደን ችግኝ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የአካባቢ ጥበቃ እና ደን ልማት ስራ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ መሰረት በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም