የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  መድረክ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው

81

አዳማ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  መድረክ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ባለሃብቶችና አምራች ተቋማት በተገኙበት በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የንቅናቄ መድረኩን በንግግር የከፈቱት  የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማው የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ነው።

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አሁንም ከ50 በመቶ አላለፈም ያሉት አቶ ታረቀኝ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ መለዋወጫዎችና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም የአመራርና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በሚፈለገው ልክ ያለመገኘት ለችግሮቹ ዋና  ዋና መንስዔዎች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማነቃቃት በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ መደገፍና ማበረታታት እንዲሁም ፋይናንስና መሬትን ጨምሮ ሌሎች ዕገዛ እንዲያገኙ ማስቻል ነው ብለዋል።


 

በዚህም ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምራት ከውጭ  የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረትና የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅንጅታዊ አመራርና አሰራርን ከማጠናከር ባለፈ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱንም  ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ከ600 በላይ ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማምረት መግባታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገው አጠቃላይ ርብርብ በተለይም የመሬት፣ ፋይናንስና ሌሎች እገዛዎችን በማድረግ 1ሺህ 500 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲመለሱ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል። 

በዘርፉ ያጋጠሙትን የፋይናንስ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የሃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው በተገቢው ስራ ላይ ያላዋሉ ባለሃብቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም