አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገትን የሚመጥን አዲስ የሥራ ባህል ተገንብቷል

220

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገትን የሚመጥን አዲስ የሥራ ባህል  መገንባቱን የከተማና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንደሙ ሴታ ገለጹ።  

የኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ መዋዕለ-ንዋይ የሚጠይቅና ቁጥጥር ካልተደረገበት ከፍተኛ አደጋና ኪሳራ የሚያመጣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡

ይህንን መገንዘብና የግንባታ ሥራዎችን መቆጣጠርም የካፒታል ወጪዎችን በመቀነስ፣ በሥራዎች መጓተት ምክንያት የሚመጡትን ተጨማሪ ክፍያዎች በመገደብና የንድፍ ለውጦችን በመከታተል ሥራው በጊዜ እንዲጠናቀቅ በማገዝ ረገድ ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለፈጣን ልማት መቀጠል አንዱ የዕድገት ምንጭ በመሆን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እሙን ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መስፋፋትና ቀልጣፋ መሆን ለአጠቃላይ የምጣኔ ኃብት ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽዖ ባሻገር ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠርና ማኅበራዊ ልማትን በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንደገለጹት፤ አገራዊ ለውጡ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ በርካታ ትሩፋት ይዞ መጥቷል።

ከዚህ ቀደም የነበረው አመለካከት ትንሽ አቅዶ ትንሽ መሥራት እና ትልቅ አቅዶ ባለቀ ጊዜ ይለቅ የሚል አመለካከት እንደነበር ገልፀዋል።

ይህም ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዳይጠናቀቁ እና ለተወሳሰበ ችግር ያጋለጠ እንደነበር ጠቁመዋል።

አገራዊ ለውጡ ትልቅ አቅዶ ትልቅ በመሥራት መርህ እነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከነበሩበት ውስብስብ ችግር ወጥተው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህም በከፍተኛ አመራሩ ደረጃ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ሥራ ቢገቡ ኢኮኖሚው ላይ በአጠቃላይ ሊያመጣ የሚችለውን ፋይዳ በመገንዘብ አቅጣጫ ተሰጥቶ በመሠራቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ጀምሮ ማጠናቀቅ ላይ በርካታ ችግር እንደነበር ገልጸው፤ ይህንን አመለካከት የሰበረ በኮንስትራክሽን ዘርፍ አዲስ ባህልን ማስተዋወቅ የተቻለበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምልክት ሊሆኑ የሚችሉ የግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ሚንስትር ዴኤታው  ተናግረዋል።

በተለይም የቱሪስት መዳረሻዎች፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በመዲናዋ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ  ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጀምረውና ተጠናቀው ለአገልግሎት ማዋል እንዲቻል ዕድል የፈጠረ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ ፕሮጀክቶች ትንንሽ እና የሚፈለገውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ያልተቻለበት እንደነበር ጠቁመዋል።

አገራዊ ለውጡ በዘርፉ ትልቅ አስቦ ትልቅ የመሥራት አመለካከትን ያመጣ ትሩፋት መሆኑን አንስተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም