ህብረቱ የጤናውን ዘርፍ ከማጠናከር ረገድ በኢትዮጵያ እየሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ

92

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 15/2016 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የጤናውን ዘርፍ ከማጠናከር ረገድ በኢትዮጵያ እየሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ፡፡

ዶክተር መቅደስ ዳባ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ዶክተር መቅደስ እንደገለጹት ህብረቱ የጤናውን ዘርፍ ከማጠናከር ረገድ በኢትዮጵያ እየሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ ነው።

በቀጣይም የማይበገር የጤና ስርዓትን ከመገንባት ረገድ፣ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና አስፈላጊውን የጤና ምላሽ መስጠት፣ ስርዓተ ፆታን በጤናው ዘርፍ ለማካተት፣ የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ህብረቱ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማብቃት እና በግጭት የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ከማቋቋምና ከመገንባት ረገድ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይም ህብረቱ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። 

በቀጣናው የላቀ የባዮ ሜዲካል ላብራቶሪን ከማስፋፋትና ከራስ አልፎ ለሌሎች ሀገራትም አቅም መሆን የሚያስችል ስራ እየተሰራ ስለሆነ ህብረቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫውን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዲያደርግም ልዑካኑን አስረድተዋል። 

የአውሮፓ ህበረት ኮሚሽን ኃላፊ ሮበርቶ ሺሊሮ በበኩላቸው ተቋማቸው ለበርካታ ዓመታት የጤናው ዘርፍ አጋር በመሆን ዘርፍ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደቆየ ገልጸዋል።

የማይበገር የጤና ስርዓትን እውን ለማድረግ እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ከማሻሻል ረገድ ተቋማቸው አስፋላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው በህብረቱ የሚደገፉ ፕሮጀክቶን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወንና ለውጣቸውንም በቅርበት እየተከታተሉ ለመገምገም የሚያስችል ስልት መንደፍ እንደሚገባውም ገልጸዋል።

የግሉን የጤና ዘርፍ ከማብቃት እና ተሳታፊ ከማድረግ ረገድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በግጭት ምክንያት የወደሙ ተቋማቶችን መልሶ ከመገንባት፣ ጾታዊ ጥቃት ላይ እና ስርዓት ፆታን ከማካተት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ከማብቃት ረገድ አበክረው እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም