የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉባቸው የተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች የሀገር ውስጥና የወጪ ንግድን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል-የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉባቸው የተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች የሀገር ውስጥና የወጪ ንግድን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል-የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፦ የውጭ ባለሃብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ መወሰኑ የሀገር ውስጥና የወጪ ንግድን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ በተከለሉ የወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ ስራዎች የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የሚፈቅድ መመሪያ ላይ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው።
ውሳኔው የወጪ ንግድን ተወዳዳሪ በማድረግ፣ ለሸማቾች አማራጮችን በማስፋትና ህጋዊ ስርአትን በማስፈን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ የውጭ ባለሃብቶች በወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ መፈቀዱ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
ባለሃብቶቹ ያላቸው ልምድ፣ ካፒታልና የስራ ክህሎት በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን አንስተው አብራርተዋል።
ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ስራ ላይ መሳተፋቸው ካላቸው የውጭ ገበያ ተደራሽነትና ትስስር አንጻር ለወጪ ንግድ ማደግና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት ለውጪ ገበያ እየቀረቡ የሚገኙ ምርቶችን በአይነትና በመጠን ከመጨመር ባለፈ አዳዲስ ምርቶችን ለማካተት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የቁም እንስሳትን ጨምሮ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ህጋዊ ስርአት በማስያዝ በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ ንግድ ምክንያት በየአመቱ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ የግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም አለም አቀፍ ተቋማት በዘርፉ እንዲሳተፉ መፈቀዱ በህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ አካላት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ምርትን በመደበቅ፣ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና ሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮችን በግብይት ስርአቱ ውስጥ በመፍጠር ሸማቹን ህብረተሰብ የሚያማርሩ ሁኔታዎች እንዳሉ አንስተዋል።
የውጭ ባለሃብቶች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ መፈቀዱ በግብይት ስርአት ውስጥ ያለውን የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማስተካከል ለዋጋ መረጋጋትና ህጋዊ ስርአት መስፈን አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
የሀገር ውስጥ ነጋዴዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግና ለሸማቹ ህብረተሰብ አማራጭን ለማስፋት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዘርዝረዋል።
መንግስት ለባለሃብቶች ፈቃድ በሚሰጥበት ወቅት ያላቸውን ታሪክ፣ አሰራርና አቅም በትኩረት መመርመር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በፋይናንስ ፖሊሲ በኩል የካፒታል ገበያ መቋቋም እንዲሁም የውጭ ባንኮች እንዲገቡ እየተደረገ ያለው ማሻሻያ ለገንዘብ አቅርቦት መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል።
በአርሲ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪና መምህር ዶክተር አደም ፈቶ በበኩላቸው ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተፈቅደው የነበሩ የንግድ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸው በምጣኔ ሃብት ላይ ዘርፈ ብዙ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል።
ውሳኔው የወጪ ንግድንና የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጨመር የመንግስት ገቢን ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ያብራሩት።
ባለሃብቶቹ በሀገር ውስጥ ችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሳተፉ መፈቀዱ በአይነትና በዋጋ አማራጭን በማስፋት ለሸማቾች አማራጭን እንደሚያሰፋ ጠቁመዋል።
ሂደቱን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በጋራ ተጠናክረው ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል የሚያስችላቸውን አማራጭ ለማየት እንደሚረዳቸው አንስተዋል።
መመሪያው ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ፣ የሀገር ምጣኔ ሃብትን የበለጠ የሚደግፉና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች ሊኖሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግስት ባለፉት ስድስት አመታት ለረዥም አመታት ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉ ለዘላቂ ምጣኔ ሃብት ግንባታና ተወዳዳሪነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል።