በሲዳማ ክልል የፕላስቲክ ውጤቶች በአካባቢ ብክለት ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል

239

ሐዋሳ፣ሚያዚያ 15/2016 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል የፕላስቲክ ውጤቶች በአካባቢ ብክለት ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ ለመከላከል ከማህበራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።

የፕላሲቲክ ውጤቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተደራጁ ማህበራት በበኩላቸው የአየር ብክለትን ለመከላከል እንደ ሀገር የተጀመረውን ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ቲቦ ለኢዜአ እንደገለጹት"ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በይፋ ተጀምሯል።

በንቅናቄው ለስድስት ወራት የሚከናወኑ የዘመቻ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ስለአካባቢ ብክለት ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ባለፈ ባለድርሻ አካለትን ንጹህና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

እንደ ሀገር የብክለት መነሻ ተብለው የተለዩ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈርና የድምጽ ብክለቶች እንዳሉ አስታውሰው፣ ብክለት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ከግምት ያስገባ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የፕላስቲክ ብክለት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል ከተደራጁ ማህበራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበራቱ በተለያዩ ከተሞች የፕላስቲክ ወጤቶችን ሰብስበው መልሶ ጥቅም ላይ መዋል በሚቻልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን የንቅናቄው አካል እንዲሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።   

ፕላስቲክ ከ500 እስከ 1000 ዓመት አፈር ውስጥ የመቆየት አቅም እንዳለው በጥናት መረጋገጡን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአካባቢ ብክለት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመከላከል የህብተረተሰቡ ድርሻ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ፕላስቲክ ቆሻሻውን ለይቶ ለተደራጁ ማህበራት በመስጠት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተጀመረውን ዘመቻ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል::

የሃዋሳ ውበት ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድና ሪሳይክሊንግ ሥራ ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ ዶንጋቶ በበኩላቸው ከ2010 ጀምሮ በተደራጀ መንገድ ቆሻሻን የመሰብሰብና ጥቅም ላይ የማዋል ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። 


 

ማህበሩ 86 ቋሚ እና ከ1ሺህ 500 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በአምስት ተሽከርካሪዎች በመታገዝ ከየቤቱ ቆሻሻ የማሰባሰብ ሥራ ያከናውናል።

ከሚሰበስቡት ቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮምፖስት ከማዘጋጀት በተጨማሪ ለአካባቢ ብክለት ተጽዕኖ ያላቸውን ፕላስቲክ ወጤቶች መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ስራ እያከናወነ ይገኛል

"ቆሻሻ ሃብት ነው" ያሉት አቶ ሄኖክ በዘፈቀደ የሚጣሉ የፕላስቲክ ምርቶችን በመሰብሰብ የሀዋሳን ሐይቅ እና አካባቢን ከብክለት ከመከላከል ባለፈ ለመልሶ ጥቅም በማዋል ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ፕላስቲክ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ማህበሩ ከክልሉ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀን ከ2ሺ 400 ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክ እንደሚሰበስቡ የገለጹት ስራ አስኪያጁ ከሃዋሳ በተጨማሪ 11 በሚደርሱ የክልሉ ከተሞች፣ በሻሻመኔና ጥቁር ውሃ ኮፈሌና ሃላባ ከተሞች እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም አንድ ኪሎ ፕላስቲክ ከ8እስከ 10 ብር እንደሚገዙ ገልጸው በዘርፉ የሚሰሩ ማህበራትን በማበራከት የአካባቢ ብክለትን መከላከልና ቆሻሻን ወደ ሃብት መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኩል ፕላሲቲክ ሪሳይክልንግ ኢንተርፕራይዝ ማህበር አስተዳዳር ክፍል ሃላፊ  ኢዮብ ኢያሱ ማህበሩ ለአካባቢ ብክለት ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ፕላስቲኮች መልሶ የመጠቀም ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡


 

በፕላስቲክ ተረፈ ምርቶቹ በዋናነት ለችግኝ መትከያ የሚሆኑ "ፖሊ ባግ" እንደሚያመርቱ ገልጸው ፖሊ ባጎቹን በአረንጓዴ ልማት ለተሰማሩ ማህበራት እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ፕላስቲክ በአካባቢ ላይ የሚያሳድረውን ብክለት ለመቀነስ ከክልሉ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብሏል፡፡

ከክልሉ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በወራት የተከፋፈሉ ስድስት ተግባራት የፕላስቲክ፣የአየር፣የውሃ፣የአፈርና የድምጽ ብክለትን ጨምሮ አካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ እስከ መጪው መስከረም የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም