በወታደራዊ ሳይንስ የተካነ ተተኪ የሠራዊት አመራር የማፍራቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

154

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የሚያስቀጥል እና በወታደራዊ ሳይንስ የተካነ ተተኪ የሠራዊት አመራር የማፍራቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ የአመራር ትምህርት ቤት ተገኝተው በስልጠና ላይ ለሚገኙ የዕዙ የበታች ሹሞች የሕይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

ኢታማዦር ሹሙ በዚህ ወቅት አሁን ላይ በመከላከያ ሰራዊቱ የሚገኙ የበታች ሹሞች ነገ ላይ የዛሬዎችን ከፍተኛ አመራሮች በመተካት መከላከያን የሚመሩ እንደሆኑ ገልጸዋል።


 

በየደረጃው በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካነ የነገይቷ ኢትዮጵያ ሠራዊት አመራሮችን የመገንባቱ ሥራ ለነገ የሚባል አይደለም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የሰራዊት አመራሮችን የማሰልጠኑ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሠልጣኝ የበታች ሹሞች የሠራዊቱ ቁልፍ መሪዎች ለመሆን በርትተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ በተፅዕኖዎች ሳይበገሩ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው የጠንካራ ሠራዊት መሠረቱ ለሀገሩ የማይደርቅ ፍቅር ያለው ጠንካራ አመራር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የዕዙ ማሠልጠኛ የክፍሉን የማድረግ አቅም ለማሳደግ ራሡ በቅቶ ሠራዊቱን የሚያበቃ አመራር የመገንባት ስራን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም