በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በእስካሁኑ ትግበራ የተሻለ ውጤት መገኘቱ ሁሉም በልማቱ እንዲሳተፍ የሚያነሳሳ ነው  

143

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 14/2016(ኢዜአ)፡- በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በእስካሁኑ ትግበራ በየአካባቢያቸው ተጨባጭ ውጤት መገኘቱ ሁሉም በልማቱ እንዲሳተፍ የሚያነሳሳ መሆኑን የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

በሀዋሳ በተካሄደው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተሳተፉ የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በመርሀ ግብሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት መታየቱን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት መሰረት በማድረግ ሁሉም በልማቱ እንዲሳተፍ የሚያነሳሳ መሆኑ ተመልክቷል።


 

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ በክልሎቹ ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ምቹ የሆነ ዕምቅ ሀብት መኖሩን ይናገራሉ።

አቶ አሻድሊ፣ የመርሃ ግብሩ ትግበራ ከተጀመረ አንስቶ በክልሉ በተለያየ መልኩ መነቃቃት መታየቱንና ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከግብዓት አቅርቦት አኳያ በዋናነት የመኖ እንዲሁም ዝርያ ለማሻሻል የሚያግዝ ንጥረ ነገር እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በግል ባለሀብቱና በክልሉ መንግስት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።


 

አቶ አወል አርባም እንዲሁ በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አተገባበር ሂደት የእውቀትና ክህሎት ውስንነት ለማቃለል ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ አተገባበር በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ ልህቀት ማዕከል ሊወሰዱ የሚችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ "ከእነዚህ አካባቢ ልምድ ይቀሰማል" ብለዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ ያሉትን አቅሞች ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተተገበረው መርሃ ግብር ውጤት እስያገኘ ነው ብለዋል።

በቀጣይም መርሃ ግብሩን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ለችግሮች ፈጣን መፍትሄ  በሚሰጥ መንገድ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በከተማ አስተዳደሩ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ውጤት የብዙ ዜጎችን ህይወት እየቀየረ ነው። 

በተሰራው ስራ በሌማት ትሩፋት የሰዎችን ህይወት ሊለውጥ የሚችል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የራሱ አስተዋጾ እንዳለውም ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከተማም ከዓሣ በስተቀር በሁሉም የሌማት ትሩፋት ዘርፎች ውጤት መገኘቱን ከንቲባዋ ገልጸዋል። 


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው "በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ሁሉም በልማቱ እንዲሳተፍ የሚያነሳሳ ነው" ብለዋል። 

መርሀ ግብሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በአርሶ አደሩ እና በአርብቶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ በቤተሰብ ደረጃም እየተተገበረ ያለ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዱ ሁሴን፣ መርሃ ግብሩ የስነ-ምግብ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ መሆኑን ያመላከተ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም መርሃ ግብሩ በውስን መሬት ላይ በርካታ ዜጎች ሌማታቸውም መሙላት እንደሚችሉ በትግበራ ሂደቱ ከተገኙ ውጤቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሲዳማ ክልልም ከግብይት ጀምሮ አጠቃላይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩን ከመምራት አንጻር የተሻለ ተሞክሮ መቀመራቸውን ተናግረዋል።

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ሀገራዊ የምክክር የግምገማ መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና ሚንስትሮች እንዲሁም ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም