የቡናና ፍራፍሬ ልማትን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ

170

ዲላ ፤ ሚያዚያ 14/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡናና ፍራፍሬ ልማትን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ጸሀይ ወራሳ አስገነዘቡ።

በክልሉ ከ60 ሚሊዮን በላይ የቡናና ፍራፍሬ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ዛሬ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል።

የክልሉ ምክት ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሃይ ወራሳ በወቅቱ እንዳሉት የክልሉን የግብርና ልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ጥረቶች መጠናከር አለባቸው።


 

በተለይ የቡናና ፍራፍሬ ልማትን ለማዘመን በተሰጠው ትኩረት መሰረት የተገኙ ውጤቶችና ተሞክሮዎችን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በይበልጥ ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ ያረጁ ቡናዎችን ነቅሎ በተሻሻሉ ዝርያዎች በመተካትና የማሳ እንክብካቤን በማጠናከር በቡና ልማት የሚስተዋሉ የምርታማነት ልዩነቶችን ማጥበብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፍራፍሬ ልማት ከምግብ ዋስትና ባሻገር ለኢንዲስትሪ ግብዓት በመሆኑ የምርት ትስስርንና ምርታማነትን ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ መልኩ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

በክልሉ በተያዘው ዓመት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ372 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ናቸው።

ከዚህ ውስጥ ከ60 ሚሊዮን የሚልቁት ቡናና ፍራፍሬ መሆናቸውን ጠቅሰው "8 ሺህ 800 ሄክታር በጉንደላና ነቅሎ ተከላን ጨምሮ 16 ሺህ ሄክታር ማሳ በቡና ልማት ይሸፈናል" ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከቡና ተከላ  ዛሬ መጀመሩንና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም ከ 32 ሚሊዮን በላይ ለመትከል ርብርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል። 

የቡና ምርትና ጥራትን ለማሳደግ የክልሉን አቅሞች ለይቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በቡና ዘር አቅርቦት መተኮሩን ተናግረዋል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው በዞኑ የቡና እድሳት ስራዎችን በስፋት በማከናወን የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ያረጀ ቡና ነቅሎ በአዲስ በመተካት ባለፉት አመታት በተከናወኑ ተግባራት በአማካይ 5 ኩንታል የሆነውን የዞኑ ምርታማነት በተያዘው ዓመት በአማካይ 9 ኩንታል እንዲሁም በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ 19 ኩንታል ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

በተያዘው ዓመት በዞኑ ከ12 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል።

በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ የተገኘውን ምርታማነት ለማስፋት የኩታ ገጠም የቡና ልማት ስራ አርሶ አደሩን የማላመድ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እቴነሽ ገብረስላሴ በበኩላቸው የቀድሞ የቡና ተክል ያረጀና በቂ ምርት የማይሰጥ በመሆኑ ነቅለው ማንሳታቸውን ተናግረዋል።

የጉድጓድ ቁፋሮና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በማድረግ ከ500 በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያ ችግኞችን መትከል መጀመራቸውን አመልክተዋል።

በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የክልልና የዞን የመንግስት ሥራ ሃላፊዎችና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም