በክልሉ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተገለጸ

180

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አባላትና ባለሙያዎች የአካባቢ ብክለት ለመከላከል የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

‘‘ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ!’’ በሚል መሪ ሃሳብ የአካባቢ ጥበቃና ብክለትን የመከላከል ዘመቻ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት፤ በአየር ንብረት ለውጥ መባባስ በየጊዜው እየተስተዋለ ያለው ድርቅ፣ ጎርፍና ረሃብ ለዜጎች ፈተና እየሆነ መጥቷል።

ለዚህም የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት ለመከላከል መንግሥት ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ያለው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።  

በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ብክለት በዘላቂነት ለመከላከል በየተቋማቱ የሚገኙ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ተገንዝበው የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።  

በተለይም በትላልቅ ከተሞች የብክለት ምንጭ የሆኑና በየቦታው የሚጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶች ለገቢ ማስገኛና ለኑሮ ማሻሻያ እንዲውሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው፤ በከተሞች የሚስተዋለው የአካባቢ ብክለት ለማስወገድ የሁሉንም አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ  እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


 

በተለይ በየቦታው የሚጣሉ ፕላስቲኮችን በቀላሉ መከላከል ካልተቻለ ኅብረተሰቡን ለከፋ የጤና ችግሮች ከማጋለጡም በላይ፤ የከተሞች ውበትና ደህንነት ችግር ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል።

ለዚህም ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ የግንዛቤ ፈጠራና የህዝብ ንቅናቄ ዘመቻ ከዚህ በፊት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ክልሉ ከአካባቢ ብክለት ነፃ፣ ምቹና ለሰው ልጆች መኖሪያ ተስማሚ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

''በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተራቆተ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ ለመተካት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተተገበረ ይገኛል'' ያሉት ደግሞ የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ ለማ ናቸው።


 

በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን የፕላስቲክ ቆሻሻን ለመከላከል የተለያዩ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎችን ማገዝና ውጤቱን ለማፅናት ትኩረት የተሰጠው ሀገራዊ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣት አይቸው ደባስ በበኩሉ፤ የወዳደቁ ፕላስቲኮችን ሰብስቦና ፈጭቶ ለተለያዩ ፋብሪካዎች እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።


 

በወር ውስጥም እስከ 40 ሺህ ኪሎ ግራም የወዳደቁ ፕላስቲኮችን በመፍጨትና በመጨፍለቅ ለፋብሪካዎች ግብዓት እንዲሆኑ  በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በመድረኩ የክልል፣ የፌዴራልና የዞን የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም