በሲዳማ ክልል የህብረት ሥራ ማህበራትን ተወዳዳሪና ተጽእኖ ፈጣሪ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ

108

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የህብረት ሥራ ማህበራት ተወዳዳሪና ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆን አስተዋጿቸውን እንዲያጠናክሩ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሳ አስታወቁ።

"የኅብረት ሥራ ማህበራትን ማዘመን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የኅብረት ሥራ ማህበራትን ለማዋሃድ፣ ለማጠናከርና ለማዘመን ታስቦ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ህብረት ሥራ ማህበራት የዜጎችን የተናጠል ጉልበት፣ ሀብትና እውቀት በማሰባሰብ የኢኮኖሚ ጉድለት ለመሙላትና የገበያ ሚዛንን ለመጠበቅ ጉልህ ድርሻ አላቸው።

በተለይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ አቅርቦት ዋንኛ ምንጭ በመሆን የሚያገለግለውን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ህብረት ስራ ማህብራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት በተለይ በብድርና ቁጠባ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ተግባራት አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሆኖም ዘርፉ አሁን ላይ ካለበት በርካታ ተግዳሮቶች መካከል የውስጥ አሰራር አለመዘመን፣ ማህበራቱ በሚፈለገው ልክ በግብይት አለመሳተፍና የካፒታል አቅማቸው ደካማ መሆን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ማህበራቱን ከተግዳሮቶቹ ለማላቀቅና በዘርፉ ሁለንተናዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሪፎርም ማካሄድ ማስፈለጉን ተናግረዋል።

"ይህም ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ ገበያን ለማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ህብረት ስራ ማህበራት ተወዳዳሪና ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስችላል" ብለዋል።

የልማትና የእድገት የሪፎርሙ ንቅናቄ የማህበራትን የውስጥ አደረጃጀት የማጠናከር፣ የፋይናንስ አቅማቸውን በማሳደግ የላቀ የገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው ጭምር ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው "በሀገሪቱ የሚገኙ  ህብረት ስራ ማህበራት አብዛኛዎቹ ከውጥ ጉድለታቸው ጋር ተያይዞ አሁናዊ  አቅምና አቋም በውስብስብ ተግዳሮቶች ተከቧል" ብለዋል።


 

በተለይ ማህበራቱ ካሉባቸው ድክመቶች መካከል የአደረጃጀት፣ የአመራርና የአሰራር ብቃት ማነስ፣  እራስን ከሁኔታዎች ጋር ማጣጣም አለመቻል እንዲሁም ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ያለመቻል ችግር ዋንኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንግሥት ተግዳሮቶቹን ለመፍታት የማህበራቱን ጥንካሬና ጉድለት በዝርዝር በመለየት የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄና የትግበራ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን አስታውቀዋል።

መንግሥት ሪፎርሙን የመምራትና ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢ የመፍጠር፣ ውጤትን መሠረት ያደረገ ድጋፍ ለማህበራቱ  የማቅረብ ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ሀጢሶ በክልሉ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ከ484 ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው 10 ዩኒየኖችና 2 ሺህ 510 መሠረታዊ ማህበራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚንቀሰቀሱት እነዚሁ ማህበራትና ዩኒየኖች በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒየኖቹና ማህበራቱ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በምርት ማሳደጊያ አቅርቦትና በገበያ ማረጋጋት ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ በስራ እድል ፈጠራ ረገድ ለ100 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።  

ከንቅናቄ መድረኩ በተጓዳኝ የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች አውደ ርዕይና ባዛር ተካሂዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም