የናይል ተፋሰስ ሀገራት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂና ፍትሐዊ የአጠቃቀም ስርዓትን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የትብብር ማዕቀፉን ሊፈርሙና ሊያጸድቁ ይገባል

162

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 14/2016(ኢዜአ)፦ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂነት ያለው ፍትሐዊ የአጠቃቀም ስርዓትን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የትብብር ማዕቀፉን እንዲፈርሙና እንዲያጸድቁ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ጥሪ አቀረበ።

የናይል ተፋስስ ኢኒሼቲቭ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኢኒሼቲቩ የተፋሰሱን ፀጋዎች በጋራ በማልማት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዓላማ አለው።

25 ዓመታትን ያስቆጠረው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በትብብር ማልማት፣ የውሃ ሀብት ስራ አመራር እና የውሃ ሀብቶች ልማት ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በቀጣናው ፈተናዎችን በመሻገር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊ አጠቃቀም እና የውሃ ሀብት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብርና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ባደረጋቸው ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞች በሃይል ትስስር በውሃ ሀብት ስራ አመራር በአቅም ግንባታ እና የህዝብ ኑሮ የሚያሻሽሉ ዉሃ ነክ በርካታ ኢንቨስትመንት ገቢራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከሌሎች ቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ፣ ስራ ፈጠራና ድህነት ቅነሳ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በሰላምና ደህንነት፣ በውሃ ዋስትና፣ በኃይል፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በምግብ ዋስትና መሰል ፈተናዎችን ለመሻገር እንደ ሀገርና እንደ ተፋሰስ በትብብር መስራት ይገባል ነው ያሉት። 

የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭን ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቀጣናዊ ተቋም ለማሸጋገርና በተፋሰሱ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂና ፍትሓዊ የውሃ አጠቃቀምን ለመምራት በፈረንጆቹ 2010 የተደረሰውን የትብብር ማዕቀፍ ያልፈረሙ አባል ሀገራት እንዲፈርሙም ጥሪ አቅርበዋል።

በማዕቀፍ ስምምነቱ መሰረት ስድስት ሀገራት ፈርመው ካጸደቁት ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ ሲሆን እስካሁን ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ፈርመውታል።

ሆኖም ያጸደቁት ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ኡጋንዳ ብቻ ሲሆኑ ወደ ትግበራ ለመግባት ሁለት ተጨማሪ ሀገራት እንዲያጸድቁት ይጠበቃል።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር) እንደሚሉት፥ የተፋሰሱ ኢኒሼቲቭ ህጋዊ ቋሚ ተቋም እንዲኖረው ማድረግና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስተዳደርን በስኬት መምራት ይገባል።

የትብብር ማዕቀፉ ከወንዝ ጉዳይ ባለፈ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ወደ ተግባር እንዲገባ መስራት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ በበኩላቸው፤ ኢኒሼቲቩ በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።


 

ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየተሳሰረች መሆኑን ገልፀው፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት ዕውን እንዲሆን አበክራ እንደምትሰራ ገልጸው፣ እስካሁን ግን መደላድል ቢፈጠርም ባላት ውሃ ሀብት ልክ ገና አልተጠቀመችም ብለዋል።

የሀገራቱ የጋራ አደረጃጀት የሆነው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ወደ ሕጋዊ ቀጣናዊ ኮሚሽን እንዲሸጋገር ያላትን ፅኑ መሻት ገልፀው፣ ሀገራቱም ስምምነቱን ማፅደቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ከራሷ አልፎ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጎርፍና ሌሎች አደጋዎችን በመቀነስ ረገድ ያላቸውን ወሳኝ አስተዋፅኦ አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ግድቦችና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂ ፍሰት ለመጠበቅ አይነተ ብዙ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እያከናወነች ስለመሆኗ አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም