10ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረም ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

106

 አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ 10ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረም  ከነገ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

“የ2030 ዘላቂ የልማት አጀንዳን እና የ2063 አጀንዳ ትግበራን ማፋጠን፣ በቀውስ ወቅት ድህነትን ማጥፋት፥ ዘላቂና የማይበገሩ የፈጠራ መፍትሔዎችን በውጤታማነት መተግበር" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

በፎረሙ ላይ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመራሮች፣  የተለያዩ ሀገራት የፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎች እና ሌሎችም የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ይሳተፋሉ።

ፎረሙን ያዘጋጁት የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከተለያዩ የተመድ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

በ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች እና አጀንዳ 2063 ትግበራ ያለበት ደረጃ፣ እድሎችና ፈተናዎች እንደሚገመግም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከዘላቂ የልማት ግቦች መካከል ድህነትን ማጥፋት፣ ረሃብን ማጥፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እርምጃ መውሰድ፣ ሰላም ፍትህና ጠንካራ ተቋማት መገንባት እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት እንዲሁም የአጀንዳ 2063 ተዛማጅ ግቦች በተለይም የሁለተኛ ምዕራፍ የ10 ዓመት እቅድ በጥልቀት እንደሚዳሰሱ ተመላክቷል።

የዘላቂ ልማት ግቦች እና አጀንዳ 2063 ተፈጻሚነትን ለማሻሻል አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም ፈጠራን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎችን መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።

በፎረሙ ላይ የዘላቂ ልማት ግቦች እና አጀንዳ 2063 አፈጻጸም ላይ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦች በፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

10ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረምን የተመለከቱ ቅድመ ስብሰባዎችና የጎንዮሽ ሁነቶች ከሚያዚያ 9 እስከ ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ሲካሄዱ ቆይተዋል።

የዘላቂ ልማት ፎረሙ እስከ ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።

9ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረም እ.አ.አ በ2023 በኒጀር ኒያሚ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም