ሆስፒታሉ ከ1 ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በዘመቻ መስጠት ጀመረ

125

ደሴ ሚያዝያ 14/016- (ኢዜአ)፤ በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ1 ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት በዘመቻ መስጠት ጀመረ።

በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለሚሰቃዩ ከ1 ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ መስጠት የተጀመረው ዛሬ ነው፡፡

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ እንደገለጹት፤ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በተጀመረው የሕክምና አገልግሎት ስድስት የዘርፉ ስፔሻላይዝድ ዶክተሮችን ጨምሮ 30 የዓይን ሐኪሞች እየተሳተፉ ናቸው።

ዛሬ ብቻ ከ600 ለሚበልጡ ሰዎች ሕክምና መሰጠቱን ጠቁመው፤ ከደሴ፣ ከኮምቦልቻን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ዜጎች በሕክምናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የሕክምና አገልግሎቱ ከሚያዚያ 14 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ጠቅሰው፤ ዘመቻው በሕክምና መዳን እየቻሉ በተለያየ ምክንያት መታከም ያልቻሉና በዓይን ሞራ ግርዶሽ እየተሰቃዩ ያሉ ወገኖችን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ህክምናውን በነፃ ከመስጠት ባሻገር የታካሚዎች የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጭዎች እንዲሸፍኑ መደረጉን አመልክተዋል።

በሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊና የዘመቻው አስተባባሪ አቶ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በወቅቱ ካልታከመ ሙሉ በሙሉ የዓይን ብርሃንን እስከማሳጣት ይደርሳል። 

ዛሬ የተጀመረው ሕክምና ቀደም ብሎ ለመታከም እድሉን ያላገኙ ወገኖችን እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

በተንታ ወረዳ የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ ንግስት ጋሹ በሰጡት አስተያየት፤ የዓይናቸው እይታ መዳከሙን ተከትሎ በቤት ውስጥ ከዋሉ አንድ ዓመት አልፏቸዋል፡፡

ዛሬ በሆስፒታሉ ነጻ ሕክምና እንዳገኙና ሙሉ በሙሉ እይታቸው ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።

የዓይናቸው የማየት አቅም በመዳከሙ በቤት ውስጥ መዋል ከጀመሩ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸው የገለፁት ደግሞ የአጅባር ከተማ ነዋሪ አቶ ይመር አሊ ናቸው።

በተደረገላቸው የነፃ ህክምና መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም እይታቸው እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለፉት አምስት ዓመታት ከ16 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የዓይን ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ከሆስፒታሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም