በዓድዋ ድል መታሰቢያ በቅርቡ አገልግሎት የጀመረው የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ምቹ እና እንግልትን እንደሚቀንስ ተጠቃሚዎች ገለጹ

119

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በቅርቡ አገልግሎት የጀመረው የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ለተጠቃሚዎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ።

በመዲናዋ ምቹ የብዙኃን ትራንስፖርት ማስተናገጃ ጣቢያዎች በብዛት አለመኖራቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ለተለያየ እንግልት ሲዳርጉ ይስተዋላል።

የትራንስፖርት ማስተናገጃዎች በብዛት መጠለያ የሌላቸው በመሆናቸው ተጠቃሚዎች ለዝናብና ፀሐይ ይጋለጣሉ፤ መሳፈሪያ ጣቢያዎቹ ብዙ ህዝብ የሚንቀሳቀስባቸው በመሆናቸው ለሌብነት ይዳረጋሉ።

በመሃል ፒያሳ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተገነባው የብዙኃን ትራንስፖርት ማስተናገጃ አገልግሎት በቅርቡ  የተርሚናል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንዳሉት፤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናል ምቹ እና በፊት የነበሩ እንግልቶችን የሚቀንስ ነው።

አቶ መስፍን ቶሎሳ  እና አቶ ይስሐቅ ሳህሌ ከዚህ ቀደም በአካባቢው አውቶብስ ለመሳፈር ብዙ እንግልት እንደነበርና ለሌቦችም ይጋለጡ እንደነበር አውስተው፥ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተገነባው ማስተናገጃ ሌብነትን ያስቀረ እና ለተገልጋዮች ምቹ የሆነ ነው ብለዋል።

ተርሚናሉ በቂ መጠለያ ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ አውቶብስ በሚጠብቅበት ወቅት ሊያጋጥመው ከሚችል ዝናብና ፀሐይ መገላገሉንም አንስተዋል።

ወይዘሮ ሂሩት ኪሮስ በበኩላቸው፥ ተርሚናሉ ዘመናዊና በቂ መቀመጫዎች ያሉት በመሆኑ ተጠቃሚዎች አውቶብስ እስኪመጣ በተረጋጋ ሁኔታ የሚጠብቁበት እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።


 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ በበኩላቸው፤  በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአብዛኛው የፒያሳ አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ ብሎም  ተጠቃሚዎች ለዝናብና ፀሐይ ሲጋለጡ እንደነበርም አውስተዋል።

አሁን ላይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የብዙሃን ትራንስፖርት ማስተናገጃ አገልገሎት መጀመሩ የነበሩ ችግሮችን ያስቀራል ብለዋል።

ተርሚናሉ ለአዛውንትና አካል ጉዳተኞችም ምቹ የሆነ፣ በቂ የደህንነት ማስጠበቂያ ካሜራዎች የተገጠሙለት መሆኑን ጠቅሰው፥ ከመንገድ ውጭ በመሆኑም የትራፊክ መጨናነቅን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን ተርሚናሉ በዘላቂነት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም