የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በመዲናዋ ያለውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ለማዘመን የሚያስችል ረቂቅ ማስተር ፕላን ይፋ አደረገ

135

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በመዲናዋ ያለውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ለማዘመን የሚያስችልና ለቀጣይ 20 ዓመታት የሚተገበር  ረቂቅ ማስተር ፕላን ይፋ አደረገ።

ኤጀንሲው ጉዳዩን በሚመለከት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡


 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት  በመዲናዋ ቆሻሻን በአግባቡና በተደራጀ መልኩ ሰብስቦ ለማስተዳደርና  መልሶ ለመጠቀም ጥናትና ምርምርን መሰረት ያደረገ  አሰራር መዘርጋት አስፈልጓል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ  በመዲናዋ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የሚተገበር  የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ረቂቅ ማስተር ፕላን መዘጋጀቱን  ጠቁመዋል።

ለረቂቅ ማስተር ፕላኑ የሚሆን ጥናት በማዘጋጀት ረገድ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን  መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ ማስተር ፕላኑ ከመዲናዋ የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ ህብረተሰቡን ባሳተፈና በተደራጀ መልኩ ሰብስቦ በማስወገድ ከተማዋን ውብ፣ፅዱና ምቹ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ይህም ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ሚናው የጎላ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

በጥናቱ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካልና ባዮ ምህንድስና  ትምህርት ክፍል መምህር ሽመልስ ከበደ (ዶ/ር) ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅት፤ በከተማዋ በቀን በአማካኝ 2 ሺህ 900 ቶን ደረቅ ቆሻሻ እንደሚመነጭ ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በአግባቡ በመሰብስብና በማደራጀት እንደሚወገድ በጥናቱ መመላከቱን ጠቅሰው፤ 12 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለተፈጥሮ ማዳበሪያና የሃብት ምንጭ መፍጠሪያ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

ቀሪው በተገቢው መንገድ እየተወገደ  አለመሆኑም ተገልጿል።

ይህም ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የቆሻሻ አወጋገድ ሰርዓትን በማዘመን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ  የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ረቂቅ ማስተር ፕላኑ በከተማዋ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲኖር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም